የሲንጋፖር ግዙፍ ባንክ 4 ሺህ ሰራተኞቹን በኤአይ ሊተካ ነው
ከ41 ሺህ በላይ ሰራተኞች ያሉት "ዲቢኤስ" በቴክኖሎጂው ምክንያት ሰራተኞቹን እንደሚቀንስ ያሳወቀ የመጀመሪያው ባንክ ሆኗል

የአለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) የሰው ሰራሽ አስተውሎት የአለማችን 40 በመቶ ስራዎች ሊነጥቅ እንደሚችል መግለፁ ይታወሳል
የሲንጋፖሩ ግዙፍ ባንክ "ዲቢኤስ" 4 ሺህ ሰራተኞቹን አሰናብቶ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (ኤአይ) ሊተካ መሆኑን አስታወቀ።
ባንኩ በቋሚነት የተቀጠሩት ሰራተኞች ቅነሳው እንደማይመለከታቸው የገለፀ ሲሆን፥ ጊዜያዊ እና የኮንትራት ሰራተኞች በቀጣይ ሶስት አመታት በኤአይ ይተካሉ ብሏል።
በአንፃሩ ከኤአይ ጋር የተያያዙ 1 ሺህ የስራ እድሎችን ለመፍጠር መታቀዱን የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፒዩሽ ጉፕታ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በእስያ አህጉር በሀብትና በቴክኖሎጂ ቀዳሚ እንደሆነ የሚነገርለት "ዲቢኤስ" በሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ምክንያት ሰራተኞቹን እንደሚቀንስ ያሳወቀ የመጀመሪያው ባንክ ሆኗል።
ባንኩ በአሁኑ ወቅት ከ8 እስከ 9 ሺህ የሚጠጉ ጊዜያዊና ኮንትራት ሰራተኞች ያሉት ሲሆን አጠቃላይ ሰራተኞቹ 41 ሺህ ይደርሳሉ ተብሏል።
የእስያው ግዙፍ ባንክ ባለፉት አስርት አመታት በኤአይ ቴክኖሎጂ ላይ በስፋት ሲሰራ መቆየቱን ዋና ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።
"በአሁኑ ወቅት ከ800 በላይ የኤአይ ሞዴሎችን አሰማርተናል፤ ይህም በ2025 745 ሚሊየን ዶላር የሚገመት ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል"ም ነው ያሉት በመጋቢት ወር የሚሰናበቱት ጉፕታ።
የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ የሰው ልጆችን ድካም ቢቀንስም የበርካቶችን ስራ የመቀማት አደጋ ደቅኗል።
የአለማቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ባለፈው አመት ባወጣው ሪፖርት ቴክኖሎጂው የአለማችን 40 በመቶ ስራዎች ሊነጥቅ እንደሚችል መግለፁ ይታወሳል።
በቴክኖሎጂው ሀገራት በእኩል ወይም ተመጣጣኝ መልኩ አለመጓዝም "የሀገራትን የእድገት ልዩነት እያሰፋ ይሄዳል" ብለዋል የአይኤምኤፍ ዋና ዳይሬክተር ክሪስቴሊና ጆርጂዮቬ።
የእንግሊዝ ባንክ ገዥ አንድሪው ቤሊ ግን ኤአይ የሰው ልጆችን ስራ ሙሉ በሙሉ የሚነጥቅ አይደለም፤ ከደቀነው አደጋ ይልቅ ይዞት የመጣው እድል መታየት አለበት ሲሉ ይከራከራሉ።