ኦፕንኤአይን ያጋለጠው ወጣት ሞቶ ተገኘ
የቀድሞው የድርጅቱ ሰራተኛ ሱቺር ባላጂ ቻትጂፒቲ ሲሰራ የቅጂ መብትን በጣሰ መልኩ ነው ማለቱን ተከትሎ ተቋሙ ክስ በዝቶበታል

የባላጂን አስተያየት ተከትሎ በርካታ ጸሃፊዎች እና አሳታሚዎች በሳን ፍራንሲስኮ በሚገኘው ድርጅት ላይ ክስ መመስረታቸው ይታወሳል
የአሜሪካውን የቴክኖሎጂ ኩባንያ "ኦፕንኤአይ" ያጋለጠው የቀድሞ የድርጅቱ ሰራተኛ ሞቶ ተገኘ።
ሱቺር ባላጂ የተባለው ወጣት ከሶስት ወራት በፊት ከሰጠው አስተያየት በኋላ ደብዛው ጠፍቶ ቆይቷል።
ሲኤንቢሲ ትናንት ይዞት በወጣው ዘገባ ባላጂ በሳን ፍራንሲስኮ በሚገኘው ቤቱ ውስጥ ሞቶ መገኘቱን አመላክቷል።
የህክምና ባለሙያዎች እና የሳን ፍራንሲስኮ ፖሊስ የ26 አመቱ ወጣት ከሳምንታት በፊት ራሱን ማጥፋቱን ተናግረዋል ይላል ዘገባው።
ለአራት አመት በኦፕንኤአይ ውስጥ በተመራማሪነት የሰራው ሲቺር ባላጂ በጥቅምት ወር ከኒውዮርክ ታይምስ ጋር ባደረገው ቆይታ ኦፕንኤአይ ቻትጂፒቲ የተሰኘውን መተግበሪያ ሲሰራ የአሜሪካን የቅጂ መብት ህግ ጥሷል በሚል መወንጀሉ ይታወሳል።
እንደ ቻትጂፒቲ ያሉ ቴክኖሎጂዎች በይነ መረብ ላይ ጉዳት ያደርሳሉ የሚሉና መሰል አስተያየቶችንም ሲሰጥ ቆይቷል።
ይህም ተቀማጭነቱን ሳን ፍራንሲስኮ ያደረገው ተቋም ከበርካታ አሳታሚዎች፣ ጸሃፊዎችና አርቲስቶች መረጃችንን ያለፈቃዳችን ተጠቅሟል የሚል ክስ እንዲያቀርቡበት ማድረጉ ነው የተነገረው።
ቻትጂፒቲን የፈጠረው ኦፕንኤአይ በበኩሉ የሚቀርብበትን የቅጂ መብት ጥሰት ክስ ያስተባብላል።
የሚሰራቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች "ለህዝብ ይፋ የሆነ መረጃ" ላይ የተመረኮዙ መሆናቸውን በመግለጽ በቀድሞው ሰራተኛው የተነሳውን ቅሬታ ውድቅ ማድረጉንም ቢቢሲ አስታውሷል።
የተቋሙ ቃል አቀባይ ከሲኤንቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ "በሱቺር ህልፈት እጅግ አዝነናል፤ ለቤተሰቦቹና ወዳጆቹ በዚህ አስደንጋጭ ወቅት መጽናናትን እንመኛለን" ብለዋል።
በቤቱ ውስጥ ሞቶ የተገኘው ሱቺር ባላጂ በነሃሴ ወር ከኦፕንኤአይ ለቆ የራሱን ፕሮጀክት እያከናወነ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።
የሞቱ መንስኤ ከቀድሞ ድርጅቱ ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።