ቻይና በአሜሪካ ላይ የጀመረችው የ”ሎሚ ወረራ” ምንድን ነው?
የቲክቶክ እናት ኩባንያ ባይትዳንስ በአሜሪካ ኢንስታግራምን የሚፎካከር “ሌመን 8” የተሰኘ መተግበሪያውን ይፋ አድርጓል
ባይትዳንስ አዲሱን የፎቶግራፍ ማጋሪያ መተግበሪያውን በስፋት ለማስተዋወቅ ከፍተኛ በጀት ይዟል ተብሏል
አሜሪካ በቻይና የቴክኖሎጂ ወረራ እየተፈጸመባት መሆኑን በተደጋጋሚ ገልጻለች፤ ይህንኑ "ወረራ" ይቀለብሳሉ ያለቻቸውን እርምጃዎችንም ስትወስድ ቆይታለች።
በቲክቶክ የተጀመረው “ወረራ” አሁን ደግሞ ወደ “ሎሚ አቢዮት” ተሸጋግሯል እያለች ነው።
ቢዝነስ ኢንሳይደር ይዞት በወጣው ዘገባ የቲክቶክ እናት ኩባንያ ባይትዳንስ ኢንስታግራምን የሚፎካከር አዲስ መተገበሪያን አስተዋውቋል።
በአሜሪካ ይፋ የተደረገው መተግበሪያ ስያሜም “ሌመን 8” መሰኘቱ ነው ዋሽንግተንን “የሎሚ ወረራ” አስነስቶብኝ ያስባላት።
የ”ሌመን 8” መተግበሪያ የሲንጋፖሩ ሄሊዮፊሊያ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ንብረት መሆኑ ተገልጿል።
ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም የወጡ ዘገባዎች አዲሱ መተግበሪያ በቻይናው ባይትዳንስ ኩባንያ መበልጸጉና ንብረትነቱም የዚሁ ኩባንያ መሆኑን አሳይተዋል ይላል ጊዝሞዶ የተሰኘ የቴክኖሎጂ ድረገጽ።
ባይትዳንስ በአሜሪካ የገጠመውን ፈተና ለማለፍ የኔ ንብረት አይደለም ማለትን መምረጡንም ዘገባው ያነሳል።
ያም ሆነ ይህ የፎቶግራም እና አጫጭር መልዕክቶች ማጋሪያ መተግበሪያው “ሌመን 8” ለዋሽንግተን ከወዲሁ ስጋት ሳይሆን አልቀረም።
የሜታ ንብረት የሆነውና ጎግል ፕሌይ ላይ ከ5 ሚሊየን በላይ ሰዎች ያወረዱት ኢንስታግራም፥ በ”ሌመን 8” ከባድ ፉክክር ገጥሞት ከገበያ ይወጣል ወይ የሚለውን ጊዜ የሚፈታው ቢሆንም የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ግን ትልቅ ትኩረት ሰጥተው እየዘገቡት ነው።
የቻይናው ባይትዳንስ አዲሱን መተግበሪያውን ለሚያስተዋውቁ በርካታ ተከታይ ላላቸው የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሜዎችም ከፍተኛ በጀት መድቦ እየሰራ መሆኑን ቢዝነስ ኢንሳይደር ዘግቧል።
በአሜሪካ ከ150 ሚሊየን በላይ የቲክቶክ ተጠቃሚ ያለው ባይትዳንስ፥ አዲሱ የፎቶግራፍ እና አጫጭር ቪዲዮ ማጋሪያ መተግበሪያው ከኢንስታግራም ጋር በብዙ መልኩ እንደሚመሳሰል ተገልጿል።
እንደ ቲክቶክም “Follow” እና “For You” የሚሉ አማራጮችና እንደየፍላጎታችን የመዝናኛ፣ ፋሽን፣ ዜና፣ ስፖርት የመሳሰሉ ፎቶ እና ቪዲዮዎችን ለማቅረብ አስቀድሞ ያስመርጠናል።
ከጉዞ እና ከውበት ጋር የተያያዙ ምክሮችን የሚሰጡ ባለሙያዎችም በ“ሌመን 8” የራሳቸው ገጽ ይኖራቸዋል ተብሏል።