ቲክቶክ ላይ ሊጣል የሚችል እገዳ ማስታወቂያ አስነጋሪዎችን ማስጨነቁ ተገለጸ
በአሜሪካ የቲክቶክ ማስታወቂያ ገቢ በዚህ ዓመት ከ6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ይደርሳል ተብሏል
ኩባንያው የተጠቃሚዎችን መረጃ ለቻይና መንግስት አሳልፎ ይሰጣል በሚል ጫና በርትቶበታል
ቲክቶክ ላይ ሊጣል የሚችል እገዳ ማስታወቂያ አስነጋሪዎችን ማስጨነቁ ተገለጸ።
በቻይና ባለቤትነት የተያዘው ቲክቶክ በአሜሪካ የብሄራዊ ደህንነት ስጋት ምክንያት እገዳ ሊጣልበት ይችላል እየተባለ ነው።
በመሆኑም ማስታወቂያ አስነጋሪዎች ከተወዳጁ የአጫጭር ተንቀሳቃሽ ምስሎች ማጋሪያ መድረክ ቲክቶክ ማረጋገጫ እየፈለጉ ነው።
የቲክቶክ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሹ ዚ ቼው ለመጀመሪያ ጊዜ በአሜሪካ ኮንግረስ ፊት ሲመሰክሩ አስተዋዋቂዎች በአመክሮ እንደሚመለከቱ የማስታወቂያ ኤጀንሲዎች ነግረውኛል ብሎ ሮይተርስ ዘግቧል።
የቲክቶክ የአሜሪካ የማስታወቂያ ገቢ በፈረንጆች 2020 ከነበረበት 780 ሚሊዮን ዶላር በዚህ ዓመት 6.83 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።
በቻይና ባይትዳንስ ባለቤትነት የተያዘው እና በወጣት ተጠቃሚዎች ዘንድ በጣም ተወዳጅ የሆነው መተግበሪያው አሁን ላይ በአሜሪካ 150 ሚሊዮን ወርሃዊ ተጠቃሚዎች አሉት ተብሏል።
ኩባንያው የአሜሪካውያን የተጠቃሚ መረጃ በቻይና መንግስት እጅ ሊወድቅ ይችላል በሚል ስጋት የባደን አስተዳደር መተግበሪያውን እንዲያግድ ግፊት ገጥሞታል።
የቲክቶክ እገዳ ጉዳይ በተደጋጋሚ ቢነገረም አብዛኛዎቹ አስተዋዋቂዎች የማስታወቂያ ወጪ እቅዶቻቸውን አልቀየሩም ተብሏል።
የቲክ ቶክ ዋና ስራ አስፈጻሚ ቼው ለህግ አውጭዎች ኩባንያው የአሜሪካን የተጠቃሚ መረጃ ለቻይና መንግስት እንደማያጋራ ያስረዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።