ቻይና በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ድምጽ ማሰማቷን እንደምትቀጥል አስታወቀች
ቤጂንግ በተመድ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ድምጽ ስታሰማ እንደነበር ገልጻለች
ቻይና ከታዳጊ ሀገራት ጋር ለመስራት ዝግጁ እንደሆነችም ገልጻለች
ቻይና በቀጣይ ጊዜያት በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ድምጽ ማሰማቷን እንደምትቀጥል የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስታወቁ።
የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ከእስያ እና ከአፍሪካ ለተውጣጡና በጄኔቫ ጉብኝት እያደረጉ ካሉ ዲፕሎማቶች ጋር ሲወያዩ ነው ይህንን ያሉት።
ዋንግ ይ ቤጅንግ ከዚህ ቀደም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ የታዳጊ ሀገራትን ድምጽ ስታሰማ መቆየቷን አንስተዋል። በቀጣይ ጊዜም ቻይና ከታዳጊ ሀገራት ጋር የበለጠ ተቀራርባ እንደምትሰራ ነው የገለጹት።
በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ የታዳጊ ሀገራት ድምጽ ማደግ እንዳለበት አንስተዋል፡፡ ታዳጊ ሀገራት በዓለም መድረክ ያለቸው ድምጽ ቀንሶ የተወሰኑ ቡድኖች ብቻ ሊቆጣጠሩት እንደማይገባም ነው የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያስታወቁት።
ቻይና ከዚህ በፊት በዓለም መድረኮች በተለይም በተመድ ውስጥ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ድምጽ ስታስተጋባ ቆይታለችም ብለዋል ዋንግ ይ።
ቻይና የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በተመለከተ ከምዕራባውያን ከፍተኛ ትችትና ወቀሳ ሲደርስባት ቆይታለች። ይሁንና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ ሀገራቸው በሰብዓዊ መብት ጉዳይ ለውጥ ማምጣቷን ገልጸው ይህንንም ለአፍሪካ እና ለእስያ ዲፕሎማቶች አስረድተዋል።
ቻይና በየትኛውም ሀገር የውስጥ ጉዳይ ያለመግባት ግልጽ አቋም እንዳላትም ሚኒስትር ዋንግ ይ ተናግረዋል። ከዚሀ ባለፈም በታይዋን ጉዳይ ቤጅንግ ምንም አይነት ድርድር እንደማታደርግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ ተናግረዋል።
ዋንግ ይ፤ አሜሪካ በቻይና አንድነት ላይ እያደረገች ላለው ትንኮሳ ቤጅንግ አስፈላጊውን ምላሽ እንደምትሰጥም ሚኒስትሩ በድጋሚ ገልጸዋል።
ከቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ ጋር ውይይት ያደረጉ የአፍሪካ እና እስያ ዲፕሎማቶች በበኩላቸው ታይዋን የቻይና አንድ አካል እንደሆነች ጠንካራ እምነት አለን ብለዋል።
ታይዋን የቻይና አካል መሆኗ በተባበሩት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ የተወሰነና ምንም የማያጠራጥር እንደሆነም ዲፕሎማቶቹ የተናገሩት።