ቻይና ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ የሠራችውን ሶስተኛውን የውጊያ መርከብ ስራ አስጀመረች
ጃፖን የቻይና የጦር መርከቦች ከ200ኪ.ሜ ርቀት ላይ መታየታቸዉን ገልጻለች
መርከቡ ቻይና የዓለም ወታደራዊ ቴክኖሎጂ መሪ የመሆን እቅዷ አንዱ አካል ነው ተብሏል
ቻይና ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ የሠራችውን ሶስተኛውን የውጊያ መርከብ ስራ ማስጀመሯን አስታዉቃለች።
በታይዋን ጉዳይ ከአሜሪካ ጋር ፍጥጫ ውስጥ ያለችው ቻይና ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ቴክኖሎጂዎች የተሰራ የጦር መርከብ ስራ ማሰጀመሯን አስታውቃለች፡፡
ይህች መርከብ ቻይና በዓለም የጦር ቴክኖሎጂ ቀዳሚ ለመሆን ያስቀመጠችው ውጥን አንዱ አካል መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ይህቺ የጦር መርከብ መሰራቷን ተከትሎ በሻንጋይ የመርከብ ማዕከል የሀገሪቱ የባህር ላይ ተዋጊ ወታደሮች ባሉበት ይፋ ተደርጋለች፡፡
በዓለም የውጊያ መርከብ ታሪክ አሜሪካ 11 መርከቦችን በመያዝ ቀዳሚ ስትሆን ቻይና ሶስት እንዲሁም እንግሊዝ ሁለት በመያዝ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ያሉ ሀገራት ናቸው፡፡
ቻይና በታይዋን እና በደቡባዊ ቻይና ባህር ይገባኛል ጉዳይ ውጥረት ውስጥ በገባችበት ወቅት ሶስተኛውን የጦር መርከብ ይፋ ማድረጓ በአካባቢው የነበረውን አለመግባባት የበለጠ ሊያከረው ይችላል የሚሉ ስጋቶች እየወጡ ነው፡፡
ከሰሞኑ ቻይና ካሏት የጦር መርከቦች ውስጥ አንዱ በሆነው ለሃሳ የጦረ መርከብ በጃፓን ባህር ላይ የረጅም ርቀት ልምምድ ማድረጓ ይታወሳል።
የኮሙኒስት ፓርቲ ጋዜጣ የሆነው ግሎበል ታይምስ ይዞት በወጣው ዘገባው፤ የቻይና ሁለተኛው ዓይነት 055 ትልቅ አውዳሚ የጦር መርከብ ባሳለፍነው ዓመት ስራ ላይ ከዋለ ወዲህ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ ግዙፍ የባሀር ላይ ልምምድ አድርጓል።
በልምምዱ ላይ ሉያንድ አይነት 052D እና ቼንግዱ አይነት 903 አውዳሚ የጦር መርከቦች መሳተፋቸውን ከስፍራው የወጡ መረጃዎች አመላክተዋል።
የጃፓን መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ ሶስቱ የቻይና የጦር መርከቦች ነጋሳኪ ከሚገኘው ፉክ ደሴት በ200 ኪሎ ሜተር ርቀት ላይ መታየታቸውን አስታውቋል።
የቻይና ባህር ኃይል በጣም አስፈሪ በሆነ ሁኔታ በርካታ የጦር መርከቦችን እየገነባ ሲሆን፤ ባለው ጦር መርከብ ብዛትም በዓለም ላይ ካሉ ግዙፍ የባህር ኃይሎች አንዱ መሆን ችሏል።