ቻይና በአስርት አመታት ውስጥ ባለስቲክ ሚሳይል ለመጀመሪያ ጊዜ አስወነጨፈች
ቻይና ተተኳሽ የያዘ ባለስቲክ ማሳይል በተሳካ ሁኔታ ወደ ፓሲፊክ ውቅያኖስ ማስወንጨፏን ገለጸች
ቻይና ከ1980 ወዲህ ወደ አለምአቀፍ የውሃ ክፍል ሚሳይል ስታስወነጭፍ ይህ የመጀመሪያዋ ነው ተብሏል
ቻይና በአስርት አመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለስቲክ ሚሳይል በተሳካ ሁኔታ ወደ ፓሲፊክ ውቅያኖስ ማስወንጨፏን ገለጸች።
ሚሳይሉ በዛሬው እለት በቤጂንግ ሰአት አቆጣጠር 8:44 የተወነጨፈ ሲሆን ያርፋል ተብሎ በተጠበቀው ቦታ ማረፉን የገለጸው የቻይና መከላከያ ሚኒስቴር ሙከራው "የተለመደ" እና "የአመታዊ ልምምዱ አካል ነው" ሲል አክሏል።
የሚሳይሉ አይነት እና የተወነጨፈበት መስመር ግልጽ ባይሆንም፣ "የሚመለከታቸው ሀገራት ሚሳይሉ ከመወንጨፉ በፊት እንደተነገራቸው" ቢቢሲ የቻይና መገናኛ ብዙሃንን ጠቅሶ ዘግቧል።
ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ ቤጂንግ እንዲህ አይነት የሚሳይል ማስወንጨፍ ሙከራ ያደረገችው 1980 በመሆኑ "የተለመደ ነው" ማለቷ አስገርሟቸዋል። የቻይና የሚሳይል ሙከራ ብዙ ጊዜ የሚካሄደው በግዛቷ ውስጥ ሲሆን ከዚህ በፊት ያስወነጨፈችው ባለስቲክ ሚሳይል ዢንግዣንግ ግዛት በሚገኘው ታክላማካን በረሃ ነበር ያረፈው።
ስለሆነም ቻይና ከ1980 ወዲህ ወደ አለምአቀፍ የውሃ ክፍል ሚሳይል ስታስወነጭፍ ይህ የመጀመሪያዋ ነው ተብሎ እንደሚታመን ዘገባው ጠቅሷል።
የጃፓን መከላከያ ሚኒስቴር እስካሁን በባህር ኃይሏ ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ገልጿል።
የጃፓን ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ኤንኤችኬ እንደዘገበው ሚኒስቴሩ "የቻይናን ጦር እንቅስቃሴ የተመለከቱ መረጃዎችን መሰብሰባችንን እና መከታተላችንን እንቀጥላለን፤ አስፈላጊ ጥንቃቄዎችንም እንወስዳለን" ብሏል።
ቻይና በ1980 የባለስቲክ ሚሳይል ሙከራ ባደረገችበት ወቅት 9070 ኪሎሜትር ተጉዞ ፓሲፊክ ውቅያኖስ ማረፍ ችሎ ነበር። ያ ሙከራ 18 የሚሆኑ የቻይና መርኮቦችን ማከተቱን እና እስካሁን ድረስ ግዙፍ ከሆኑት የቻይና ሙከራዎች አንዱ ተደርጎ ይወሰዳል።
ቻይና ሙከራው ከየትኛውም ሀገር ጋር እንደማይገናኝ ብትገልጽም፣ የራሷ ግዛት አድርጋል ልትጠቀልላት ከምትፈልጋት ታይዋን ጋር ፍጥጫ ወስጥ ከገባች ቆይታለች።
በቤጂንግ እና በዋሽንግተን መካከል ያለው ግንኙንት ባለፈው አመት የተሻሻለ ቢሆንም፣ ቻይና በቀጣናው የበላይ ለመሆን የምታደርገው እንቅስቃሴ የውጥረት ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል።
ቤጂንግ በታይዋን ላይ ያላት የይገባኛል ጥያቄ ሌላኛው የውጥረት ምንጭ ነው።የታይዋን መከላከያ ሚኒስቴር ቻይና በቅርቡ ተከታታይ የሚሳይል ሙከራ እና ሌሎች ልምምዶችን ማድረጓን ገልጿል።