ሰሜን ኮሪያ አሜሪካ መድረስ የሚችል ባለስቲክ ሚሳኤል ወደ ጃፓን አስወነጨፈች
የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዬ ኪሺዳ፥ የፒዬንግያንግን ፀብ አጫሪ ድርጊቷ አንታገስም ብለዋል
የአሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ያስቆጣት ሰሜን ኮሪያ ግን ፀብ አጫሪዎቹ ሶስቱ ሀገራት ናቸው ብላች
ሰሜን ኮሪያ ወደ ጎረቤቶቿ ሚሳኤል ማስወንጨፏን ቀጥላበታለች።
ትናንት ወደ ደቡብ ኮሪያ አጭር ርቀት የሚጓዝ ሚሳኤል የወረወረችው ፒዬንግያንግ ዛሬ ደግሞ ወደ ጃፓን አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤል ማስወንጨፏ ተሰምቷል።
የጃፓን መከላከያ ሚኒስትር ያሱካዙ ሃማዳ እንዳስታወቁት፥ የባለስቲክ ሚሳኤሉ 1 ሺህ ኪሎሜትሮችን ተጉዞ ኦሽማ ከተሰኘው ደሴት በስተምዕራብ 200 ኪሎ ሜትሮችን ርቆ አርፏል።
የባለስቲክ ሚሳኤሉ እስከ 15 ሺህ ኪሎሜትር ድረስ መምዘግዘግ የሚችል መሆኑን ነው ሚኒስትሩ ያነሱት።
ይህም ሰሜን ኮሪያ ባላንጣዋን አሜሪካ ማጥቃት የሚያስችላት አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤል መሞከሯን ያሳያል።
የሬውተርስ ዘገባ ግን ሚሳኤሉ አህጉር አቋራጭ ስለመሆኑ ጥርጣሬ እንጂ ማረጋገጫ አልተገኘም ብሏል።
በታይላንድ እየተካሄደ በሚገኘው የእስያ ፓስፊክ የኢኮኖሚ ትብብር ጉባኤ እየተሳተፉ የሚገኙት የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዬ ኪሺዳም ሚሳኤሉ እንደተወነጨፈ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጥታ በተላለፈ መግለጫቸው፥ ሰሜን ኮሪያ ከተደጋጋሚ ፀብ አጫሪ ድርጊቷ ትቆጠብ ዘንድ አሳስበናታል ብለዋል።
ይህን መሰሉን ድርጊቷን አንታገሳትም ያሉት ኪሺዳ ሊወሰድ ስለሚችል የአፃፋ እርምጃ ግን የጠቀሱት ነገር የለም።
የደቡብ ኮሪያ መከላከያ ሚኒስቴርም ዛሬ ወደ ጃፓን የተወነጨፈው ሚሳኤል የኒዩክሌር አረር ሊሸከም የሚችል አህጉር አቋራጭ ሚሳኤል ሊሆን እንደሚችል ገልጿል።
ፒዬንግያንግ ትናንት ወደ ደቡብ ኮሪያ ዛሬ ደግሞ ወደ ጃፓን ሚሳኤል ያስወነጨፈችው አሜሪካ ከጎረቤቶቿ ደቡብ ኮሪያና ጃፓን ጋር ወታደራዊ ልምምድ ማድረጓን ተከትሎ ነው።
የአሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን መሪዎች ባለፈው ሳምንት በካምቦዲያ ያደረጉት ምክክርም ፒዬንግያንግን አስቆጥቷል።
በካምቦዲያው የሶስትዮሽ ስብሰባ አሜሪካ ሁለቱን አጋሮቿን ከሰሜን ኮሪያ ለመጠበቅ እስከ ኒዩክሌር ማስታጠቅ ቃል መግባቷም በኪም ጆንግ ኡን ሀገር ግልፅ የጦር አዋጅ ተደርጎ ተወስዷል።
የሰሜን ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቾይ ሰን ሁይ በሰጡት መግለጫም፥ የሶስትዮሽ ምክክሩም ሆነ የጦር ልምምዱ ለሀገራቱ ጦስ ይዞ እንደሚመጣ ዝተዋል።
አጋሮቿን በማስተባበር የኮሪያ ልሳነ ምድርን እያወከች ነው ባለቻት አሜሪካ ላይም ሀገራቸው ከባድ እርምጃ እንደምትወስድ ማስጠንቀቃቸውን አሶሼትድ ፕረስ አስታውሷል።
በፈረንጆቹ 2021 ስምንት ጊዜ የባለስቲክ መሳሪያ የተሞከረችው ፒዬንግያንግ፥ ሊጠናቀቅ ሁለት ወራት በቀረው 2022 ወደ 34 እንዳሳደገችው መረጃዎች ያሳያሉ።
ይህም ሀገሪቱ የኒዩክሌር መሳሪያን ጥቅም ላይ ለማዋል ጥቂት አመት እንደቀራት አሜሪካና አጋሮቿ እያሳሰቡ ነው።