ሰሜን ኮሪያ በርካታ ባለስቲክ ሚሳኤሎችን አስወነጨፈች
የፒዮንግያንግ አጭር ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎች በደቡብ ኮሪያ ምስራቃዊ የውሃ ዳርቻ መውደቃቸው ተገልጿል
ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን የሰሜን ኮሪያ ድርጊት የኮሪያ ልሳነ ምድርን ይበልጥ ውጥረት ውስጥ የሚከት ነው በሚል ተቃውመዋል
ሰሜን ኮሪያ ዛሬ ጠዋት በርካታ “አጭር ርቀት ተምዘግዛጊ” ሚሳኤሎችን ማስወንጨፏን ደቡብ ኮሪያ ገልጻለች።
ከፒዮንግያንግ አቅራቢያ የተተኮሱት ባለስቲክ ሚሳኤሎች 300 ኪሎሜትሮችን ከተጓዙ በኋላ ወደ ምስራቃዊ የደቡብ ኮሪያ የባህር ዳርቻ መግባታቸውንም ነው ያስታወቀችው።
ጃፓንም የፒዮንግያንግን የባለስቲክ ሚሳኤል ሙከራ አረጋግጣለች።
የጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ፥ የአውሮፕላኖች እና መርከቦችን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ መረጃዎች በፍጥነት እንዲሰበሰቡ አዟል።
ሰሜን ኮሪያ ባለፉት ወራት እያካሄደችው ያለው የሚሳኤል ሙከራ የኮሪያ ልሳነ ምድር ውጥረትን ይበልጥ ያባብሳል ያሉት ቶኪዮ እና ሴኡል ከአጋራቸው ዋሽንግተን ጋር ትብብራቸውን አጠናክረዋል።
ፒዮንግያንግ በበኩሏ እንደ ሩሲያ እና ቻይና ካሉ ሀገራት ወዳጅነቷን እያጠናከረች አለማቀፍ ጫናውን ለመቀነስ ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች።
በህዳር ወር 2023 የመጀመሪያዋን የስለላ ሳተላይት በተሳካ ሁኔታ ያመጠቀችው ሰሜን ኮሪያ በቅርቡ ሁለተኛ ሳተላይት ለማምጠቅ መዘጋጀቷን ደቡብ ኮሪያ አስታውቃለች።
ባለፈው አርብ የሞከረችው “ግዙፍ” ክሩዝ ሚሳኤልና አዲስ ጸረ አውሮፕላን ሚሳኤልም ለጎረቤቶቿ ስጋት ፈጥሯል።
ፒዮንግያንግ በሚያዚያ ወር መጀመሪያም “ሃውሶንግ -16ቢ” የተሰኘና ጠጣር ነዳጅ የሚጠቀም አህጉር አቋራጭ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል መሞከሯ የሚታወስ ነው።
አረሩን ለማስወንጨፍ ጠጣር ነዳጅ የሚጠቀመው “ሃውሶንግ -16ቢ” አሜሪካን ጨምሮ “በየትኛውም አለም የሚገኙ የሰሜን ኮሪያ ጠላቶች”ን በፍጥነትና በሃይል መምታት ይችላል፤ በጸረ ሚሳኤል የመመታት እድሉም ዝቅተኛ ነው መባሉ አይዘነጋም።
አሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን የሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ሙከራው የጸጥታው ምክርቤት እገዳን የጣሰ ነው ቢሉም ፒዮንግያንግ ግን እገዳው ሉአላዊነቴን የሚጥስ እና ራሴን ከአደጋ የመከላከል መብቴን የሚገድብ ነው ትላለች።
የኪም ጆንግ ኡን አስተዳደር ሀገራቱ የሚያደርጉትን ወታደራዊ ልምምድ በሚሳኤል መቃወማቸውንም ቀጥለዋል።
ሩሲያ ባለፈው ወር የመንግስታቱ ድርጅት በፒዮንግያንግ የኒዩክሌር እና ሚሳኤል ፕሮግራም ላይ የጣላቸው ማዕቀቦች በየአመቱ እንዲገመገም የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቷን ተጠቅማ ውድቅ ማድረጓ ይታወሳል።