የታይዋን መከላከያ ሚኒስቴር በደሴቷ ዙሪያ ጦሩን ማሰማራቱንና የግዛቱን ደህንነት እንደሚያስጠብቅ አስታውቋል
ቻይና በታይዋን ሰርጥና በታይፒ ቁጥጥር ስር ባሉ ደሴቶች ዙሪያ ግዙፍ የጦር ልምምድ ማካሄድ ጀመረች።
አዲሱ የታይዋን ፕሬዝዳንት ሊ ቺንግ ቲ በዓለ ሲመታቸው ከተካሄደ በኋላ የተጀመረው ወታደራዊ ልምምድ አዲሱን አስተዳደር ለማስጠንቀቅ ያለመ ነው ተብሏል።
ቻይና የውጭ ሃይላት በደሴቷ ዙሪያ የሚያደርጉትን ጣልቃገብነት የማያቆሙ ከሆነም “ጠንካራ እርምጃ” እንወስዳለን ስትል አስጠንቅቃለች።
ቤጂንግ “አስገንጣይ” እያለች የምትገልጻቸው ፕሬዝዳንት ቺንግ ቲ በበዓለ ሲመታቸው ወቅት ያደረጉት ንግግርም የሺ ጂንፒንግ አስተዳደርን ማስቆጣቱን ሬውተርስ ዘግቧል።
የታይዋኑ ፕሬዝዳንት ቻይና በደሴቷ ላይ የደህንነት ስጋት መፍጠሯን እንድታቆም በጠየቁበት ንግግራቸው የታይዋን እጣፈንታ በህዝቦቿ ፍላጎት እንጂ በቤጂንግ አይወሰንም ነው ያሉት።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ በታይፒ ጉዳይ መላው የቻይና 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ህዝብ ወሳኝ ድርሻ አለው በሚል የፕሬዝዳንቱን ንግግር ተቃውሟል።
ሲሲቲቪም የአዲሱ ፕሬዝዳንት ንግግር በታይዋን ሰርጥ ሰላምና ደህንነትን ሳይሆን ብጥብጥን እንደሚያስከትል በመጥቀስ ቤጂንግ በዛሬው እለት የጀመረችው ልምምድ ፈጣን እርምጃ ለመውሰድ እንደሚያስችላት ጠቁሟል።
ልምምዱ እግረኛ ጦሩን፣ የባህር እና አየር ሃይሉን ያካተተ ሲሆን፥ በታይዋን ሰርጥና በአራት ታይፒ በተቆጣጠረቻቸው ደሴቶች ዙሪያ ነው እየተካሄደ ያለው።
ቻይና ልምምድ ወደሚደረግባቸው አካባቢዎች ሚሳኤሎችን የጫኑ በደርዘን የሚቆጠሩ አውሮፕላኖች እና የጦር መርከቦችን መላኳን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
“የጋራ ሰይፍ 2024ኤ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ግዙፍ የጦር ልምምድ ለሁለት ቀናት ይካሄዳል የተባለ ሲሆን፥ ስያሜው ልምምዱ ቀጣይነት እንዳለው አመላካች ነው።
የታይዋን መከላከያ ሚኒስቴር ቻይና የጀመረችውን ወታደራዊ ልምምድ ያወገዘው ሲሆን፥ ልምምድ በተጀመረባቸው አካባቢዎች ጦሩን አሰማርቶ በተጠንቀቅ እየተጠባበቀ መሆኑን ገልጿል።
ልምምዱ የታይዋን ሰርጥን ሰላምና መረጋጋት ከማናጋት ባለፈ የቻይናን የጦረኝነት አስተሳሰብ ያመላክታል ያለው ሚኒስቴሩ፥ የደሴቷን ደህንነት እንደሚያስጠብቅ አስታውቋል።
የፕሬዝዳንት ሊ ቺንግ ቲ ጽህፈት ቤትም በቻይና ወታደራዊ ልምምድ የደሴቷ ነዋሪዎች ስጋት እንዳይገባቸው ነው የመከረው።
ቻይና በ2022 እና 2023 በታይዋን አቅራቢያ ግዙፍ የጦር ልምምዶችን ማድረጓ ይታወሳል።
የቀድሞዋ የአሜሪካ ምክርቤት አፈጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ በነሃሴ ወር 2022 በታይዋን ጉብኝት ማድረጋቸውን ተከትሎም ለአራት ቀናት ያለማቋረጥ የተደረገው ልምምድ ቤጂንግ እና ታይፒን በቀጥታ ጦርነት ውስጥ ያስገባል ተብሎ ተሰግቶ ነበር።