ታይዋን በራሷ አቅም የሰራቻቸውን ባህር ሰርጓጅ መርከቦች ይፋ አደረገች
ታይፒ በይፋ ያስተዋወቀቻቸው ስምንት ባህር ሰርጓጅ መርከቦች ከሁለት አመት በኋላ ወደ አገልግሎት ይገባሉ ተብሏል
ቻይና የሉአላዊ ግዛቴ አካል ናት ወደምትላት ታይዋን በየቀኑ ጄቶቿን እየላከች ነው
ታይዋን በራሷ አቅም የሰራቻቸውን ባህር ሰርጓጅ መርከቦች ይፋ አደረገች።
የታይዋን ፕሬዝዳንት ሳይ ኢንዌን የደሴቷን የመከላከያ አቅም ያጠናክራሉ የተባሉትን ባህር ሰርጓጅ መርከቦች አስተዋውቀዋል።
ፕሬዝዳንቷ በይፋ ያስተዋወቋቸው ስምንት ባህር ሰርጓጅ መርከቦች በሁለት አመት ውስጥ ወደ ስራ እንደሚገቡም ነው የተገለጸው።
“ከዚህ በፊት በሀገር ቤት ባህር ሰርጓጅ መርከቦችን መስራት የማይቻል ይመስል ነበር፤ አሁን ግን በራሳችን አቅም ዲዛይን ተደርገው የተሰሩ መርከቦችን በአይናችን መመልከት ችለናል” ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ሳይ ኢንግዌን።
መርከቦቹን መስራቱ የራሱ ፈተና ቢኖረውም የደሴቷን ራስን በመከላከያው ዘርፍ የመቻል ጥረት ለማሳካት መሰል እርምጃዎችን መውሰድ የግድ መሆኑንም ነው ያነሱት።
ታይዋን በ1980ዎቹ ከኔዘርላንድስ የገዛቻቸውን ሁለት ባህር ሰርጓጅ መርከቦችን የሚቀላቀሉት አዳዲሶቹ ታይዋን ሰራሽ መርከቦች የደሴቷን የባህር ሃይል ይበልጥ እንደሚያጠናክሩ ይጠበቃል።
ታይፒ የባህር ሰርጓጅ መርከቦቹን በመስራት ረገድ ከተለያዩ ሀገራት ልምዶችን መቅሰሟን ብትገልጽም የትኞቹ ሀገራት ድጋፍ እንዳደረጉላት ግን አልጠቀሰችም።
የታይዋን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆሴፍ ው በታይፒ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ከቻይና የሚደርሰው ጫና እየተበራከተ መሄዱንና የደሴቷን ወታደራዊ አቅም ማሳደጉ አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል።
ታይዋንን እንደ ሉአላዊ ሀገር በመቁጠር የመሳሪያ ሽያጭ ያጸደቀችው አሜሪካ የባህር ሰርጓጅ መርከቦቹ በይፋ ሲተዋወቁ ባለስልጣኗን መላኳን ሬውተርስ አስነብቧል።
ታይፒ ሚሳኤል የሚታጠቁትን ባህር ሰርጓጅ መርከቦች ከ2025 ጀምሮ ወደ ስራ ለማስገባት አቅዳለች።
እያንዳንዳቸው 1 ነጥብ 53 ቢሊየን ዶላር ያወጣሉ የተባሉት መርከቦች ጥቃት ለማድረስ የአሜሪካውን ሎክሄድ ማርቲን ኩባንያ ቴክኖሎጂ እንደሚጠቀሙ ተገልጿል።
ባህር ሰርጓጅ መርከቦቹ በቀጣይ ወር ሙከራ እንደሚያደርጉ የተገለጸ ሲሆን፥ ቤጂንግ እስካሁን ስለአዳዲሶቹ መርከቦች መግለጫ አላወጣችም።
በተያያዘ ቻይና የሉአላዊ ግዛቴ አካል ናት ወደምትላት ታይዋን በየእለቱ የጦር ጄቶቿን እየላከች መሆኑን ታይፒ ገልጻለች።