ታይዋን በቻይና “አደገኛ አስገንጣይ” የሚል ስም የወጣላቸውን ፕሬዝዳንት መረጠች
ደሴቷ ባካሄደችው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የ64 አመቱ ዊሊያም ሌይ ቺንግቲ መመረጣቸው ይፋ ተደርጓል
የምርጫው ውጤት የታይዋን ሰርጥ ውጥረትን ዳግም እንዲያገረሽ ሊያደርገው እንደሚችል ተገልጿል
በታይዋን በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የገዥው ዲሞክራቲክ ፕሮግረሲቭ ፓርቲ(ዲፒፒ) ተወካዮች አሸንፈዋል።
የ64 አመቱ ዊሊያም ሌይ ቺንግቲ እና አጣማሪያቸው ሃሲዮ ቢክሂም ከ40 በመቶ በላይ ድምጽ በማግኘት ማሸነፋቸው ይፋ ተደርጓል።
መምረጥ ከሚችሉ 19 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎች ውስጥ 70 በመቶው ድምጽ በሰጠበት ምርጫ ከዶክተርነት ወደ ፖለቲካው የተቀላቀሉት ዊሊያም ሌይ ቺንግቲ ታይዋንን በፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ ተመርጠዋል።
የገዥው ዲፒፒ ፓርቲ ተወካይ እንዳይመረጥ በብርቱው ስትወተውት የቆየችው ቤጂንግ፥ ሌይ ቺንግቲን “ችግር ፈጣሪው” እና አደገኛው ‘አስገንጣይ” እያለች ስትጠራቸው ቆይታለች።
ሌይ ቺንግቲን ታይዋን የሉአላዊ ግዛቴ አካል ናት የምትለው ቻይና ታይፒን ወደ እናት ምድሯ ቻይና ለማዋሃድ የምታደርገውን ጥረት እንደሚፈትነው ተገልጿል።
ይሁን እኝጂ ተመራጩ ፕሬዝዳንት ከምርጫው ውጤት ይፋ መደረግ በኋላ ባደረጉት ንግግር የቤጂንግ ጋር መካረር ውስጥ የሚከቱ ሳይሆን ትብብርና ንግግርን ያስቀደሙ የተመረጡ ቃላትን ተጠቅመዋል።
በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት “የታይዋንን ነጻነት ማወጅ አይጠበቅብንም፤ ምክንያቱም ታይዋን ቀድሞም ነጻና ሉአላዊ ሀገር ናት” ያሉት ተመራጩ ፕሬዝዳንት በትናንቱ ንግግራቸው ግን ውጥረት የሚያባብስ ንግግር ከማድረግ ተቆጥበዋል።
በምርጫው አብረዋቸው የተፎካከሩት ሃሲዮ ቢክሂም ቢሆኑ በቤጂንግ የሚጠሉና ወደ ቻይናና ሆንግ ኮንግ እንዳይገቡ የታገዱ ናቸው።
የታይዋን ዲሞክራቲክ ፕሮግራሲቭ ፓርቲ ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን ማሸነፉ ከፈረንጆቹ 2016 ጀምሮ ከቻይና ጋር የተቋረጠውን መደበኛ ግንኙነት ለማደስ አስቸጋሪ ይሆናል ይላል የአሶሼትድ ፕረስ ዘገባ።
ቤጂንግ በወቅቱ ከደሴቷ ጋር ግንኙነቷን ያቋረጠችው የቀድሞዋ የታይዋን ፕሬዝዳንት ሳይ ኢንግ ዌን ታይፒ የቻይና ግዛት አካል መሆኗን ለማወጅ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ነበር።
የትናንቱ የምርጫ ውጤትም በታይዋን ሰርጥ ዳግም ውጥረቱን እንደሚያባብሰው ይጠበቃል።
ቤጂንግ እስካሁን ስለምርጫው ውጤት አንድምታ መግለጫ ባታወጣም እንደቀድሞው ግዙፍ ወታደራዊ ትርኢት በማድረግና ወደ ታይዋን የጦር መርከቦቿን በማስጠጋት ቁጣዋን ልትገልጽ እንደምትችል ነው እየተነገረ ያለው።
የቤጂንግ የጦር አውሮፕላኖችም የታይፒን የአየር ክልል ጥሰው በመግባት ልምምድ ሊያደርጉ ይችላሉ ተብሏል።