ባለፈው አመት ሳኡዲና ኢራንን ያደራደረችው ቻይና በመካከለኛው ምስራቅ የአሜሪካን ተጽዕኖ ለመገዳደር ጥረት እያደረገች ነው
ቻይና የፍልስጤም ተቀናቃኝ ቡድኖች የሆኑትን ሃማስ እና ፋታህ ማደራደር ጀመረች።
የሁለቱ ቡድኖች ተወካዮች በቤጂንግ ያደረጉት የመጀመሪያው ንግግር “ተስፋ ሰጪ” ውጤት የታየበት መሆኑንም የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሊ ጂያን ተናግረዋል።
ቃልአቀባዩ በእለታዊ ጋዜጣዊ መግለጫቸው ዝርዝር ጉዳዮችን ባይጠቅሱም የሃማስና ፋታህ ተወካዮች በቻይና ጋባዥነት ቤጂንግ በመገኘት ልዩነታቸውን ለማጥበብ ጥልቅ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
“ሁለቱም አካላት የፍልስጤማውያንን አንድነት ለማረጋገጥና ጥምረት ለመፍጠር ተከታታይ ውይይቶችን ለማድረግ ተስማምተዋል”ም ነው ያሉት።
ቤጂንግ የፍልስጤማውያንን ውስጣዊ አንድነት ለማጠናከርና የረጅም ጊዜ ነጻ ሀገር የመመስረት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የምታደርገው ጥረት በሃማስም ሆነ በፋታህ ተወካዮች መደነቁን መግለጻቸውንም አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
ለእስራኤል ነጻ ሀገርነት እውቅና መስጠት የማይፈልገውና በስድስት ቀናቱ ጦርነት በእስራኤል በሃይል የተያዙ ቦታዎች ተለቀው ነጻዋ ፍልስጤም ትመሰረታለች የሚለው ሃማስ ከእስራኤል ጋር የሰላም ስምምነት ከተፈራረመው የማህሙድ አባሱ ፋታህ ጋር ግንኙነቱ የሻከረ ነው።
በተለይ በፈረንጆቹ 2006 በተካሄደው ምርጫ ሃማስ ማሸነፉን ተከትሎም ዌስትባንክን ከሚያስተዳድረውና ፋታህ ከተቆጣጠረው የፍልስጤም አስተዳደር ጋር ልዩነቱ መስፋቱ ይታወሳል።
ሁለቱ ቡድኖች ተከታታይ ድርድር አድርገው የአንድነት መንግስት ለመመስረት መስማማታቸውም አይዘነጋም።
ስምምነቱ ሃማስ የፍልስጤም አስተዳደር ከእስራኤል ጋር የደረሰውን የሰላም ስምምነት እንዲያከብር የሚያደርግ ቢሆንም ለእስራኤል ሉአላዊ ሀገርነት እውቅና ያልሰጠበት በመሆኑ እስራኤልና አሜሪካ የአንድነት መንግስቱን እውቅና አንሰጠውም ብለው ኢኮኖሚያዊ ማዕቀቦችን ጥለው ነበር።
ይህም የሃማስና ፋታህ የአንድነት መንግስት በአጭር ጊዜ እንዲፈርስና ግጭት እንዲቀሰቀስ ምክንያት መሆኑ ይታወሳል።
እስራኤልና ምዕራባውያን አጋሮቿ ሃማስን በሽብርተኝነት በመፈረጅ ዌስትባንክን ለሚያስተዳድረው ፋታህ ደግሞ አለማቀፍ እውቅና በመስጠት የፍልስጤም የነጻነት ትግልን በሁለት ጎራ እንደከፈሉት ይነገራል።
ሰባተኛ ወሩን በያዘው የጋዛ ጦርነት አሜሪካና ሌሎች ምዕራባውያን ሀገራት ለቴል አቪቭ የሚያደርጉት ወታደራዊ ድጋፍ በፍልስጤማውያን ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ስትኮንን የቆየችው ቻይና ለፍልስጤም ነጻ ሀገርነት እውቅና ትሰጣለች።
የፍልስጤም ተቀናቃኝ ሃይሎችን በማደራደር የመካከለኛው ምስራቅ ፖለቲካ በምዕራባውያን ብቻ መዘወሩ ሊያበቃለት ይገባል ብላለች።
ቤጂንግ ባለፈው አመት ሳኡዲ አረቢያ እና ኢራንን በማደራደር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ዳግም እንዲጀምሩ ያደረገችው ስኬታማ ጥረትም ሁነኛ ማሳያ ነው።