የአለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ምንድን ነው፤ የእስራኤል ባለስልጣናትንስ ለምን አስጨነቀ?
በፈረንጆቹ 2002 የተቋቋመው ፍርድ ቤቱ 126 አባል ሀገራት አሉት
ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ ላይ የእስር ማዘዣ ሊያወጣ መሆኑ ተገነግሯል
የእስራኤል ባለስልጣናት የአለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በሀገሪቱ መሪዎች ላይ የእስር ማዘዣ ሊሰጥ ይችላል የሚል ስጋት አድሮባቸዋል።
ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት የእስራኤል ሃማስ ጦርነትን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን ጨምሮ በእስራኤል ከፍተኛ አመራሮች እና የሃማስ መሪዎች ላይ የእስር ማዘዣ ሊያወጣ እንደሚችል ተገልጿል።
እስራኤል በ126 ፈራሚ ሀገራት የተቋቋመው ዓለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት አባል ባትሆንም በጠቅላይ ሚንስትሯ እና ጦር አመራሮቿ ላይ የእስር ማዘዣ ሊወጣባቸው እንደሚችል በማሰብ ይህ እንዳይሆን በእንቅስቃሴ ላይ መሆኗ ተገልጿል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በኤክስ የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ “ዓለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ተፈጥሯዊ የሆነውን ራስን የመከላከል መብትን ለመናድ የሚያደርገውን ማንኛውንም ሙከራ በፍጹም አንቀበልም” ብለዋል።
ኔታንያሁ አክለውም "የዓለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይሲሲ) ውሳኔ በእስራኤል ላይ ተጽእኖ ባይኖረውም፤ አደገኛ ምሳሌ ይሆናል" ሲሉም ገልጸዋል።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ላይ እንደገለፀው ፍርድ ቤቱ የእስራኤል ከፍተኛ የፖለቲካ እና ወታደራዊ ባለስልጣናትን የእስር ማዘዣ ሊያወጣ እንደሚችል መሰረ እንደረሰው ለውጭ ሚሲዮኖች ማሳወቁን ተግሯል።
ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ምንድን ነው?
አለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ የጦር ወንጀሎችን፣ በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን፣ የዘር ማጥፋት ወንጀልን እና የጥቃት ወንጀሎችን ለፍርድ ለማቅረብ በፈረንጆች 2002 ተቋቁሟል።
በአባል ሀገራት ዜጎች ወይም በአባል ሀገራት ግዛት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን በመመርመር ክስ ማቅረብ ይችላል። 126 አባል ሀገራት ያሉት ሲሆን፤ የ2023 በጀቱ 170 ሚሊዮን ዩሮ ገደማ ነው።
ምንም የፖሊስ ኃይል የሌለው ፍርድ ቤቱ፤ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው እንዲቀርቡ የአባል ሀገራቱ ላይ ጥገኛ ሆኖ የሚሰራ ሲሆን፤ ይህም የፍር ሂደቱ ላይ ከፍተኛ እንቅፋት እንደሆነበት ይነገራል።
በፍርድ ቤቱ በአሁኑ ወቅት 17 ያክል ወንጀሎች የምርመራ ሂደቶች ያሉ ሲሆን፤ በአጠቃላይ 32 የእስር ማዘዣ አውጥቶ 21 ተጠርጣሪዎችን ወደ እስር ቤት ማስገባት ችሏል።
የፍርድ ቤቱ ዳኞች እስካሁን በተሰየሙበት ችሎቶች በ10 ተጠርጣሪዎች ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ሲያሳልፉ፤ አራቱን በነፃ አሰናብተዋል።