ፋታህ ኢራን በዌስትባንክ ሁከት ለመፍጠር እየሞከረች ነው ሲል ወቀሰ
ዌስትባንክን የሚያስተዳድረው ፓርቲ ነጻ ሀገር የመመስረት ትግላችን የውጭ ሀይሎች መጠቀሚያ እንዲሆን አንፈቅድም ብሏል
ፋታህ ጋዛን ከሚያስተዳድረው ሃማስ ጋር በ2007 ግጭት ውስጥ መግባቱ ይታወሳል
የፍልስጤሙ ዋነኛ የፖለቲካ ፓርቲ ፋታህ ኢራን በዌስትባንክ ሁከት ለመፍጠር እየሞከረች ነው ሲል ወቀሰ።
ከፍልስጤማውያን ፍላጎት ውጭ የሆነ አጀንዳ የሚያራምዱ የውጭ ሃይሎችን እንደሚቃወምም ነው ያስታወቀው።
ዌስትባንክን የሚያስተዳድረው ፋታህ “ቅዱስ አላማችን እና የህዝባችን ደም ለሌሎች መጠቀሚያ እንዲሆን አንፈቅድም” ሲልም ቴህራንን የሚቃወም መግለጫ አውጥቷል።
በዌስትባንክ የጸጥታ ሃይሎችና ብሄራዊ ተቋማት ላይ ለሚያነጣጥሩ የውጭ ጥቃቶችም አጻፋዊ ምላሽ እንደሚሰጥ ገልጿል።
እስራኤል የቀጠናው ዋነኛ ባላንጣዋ ኢራን ለፍልስጤም ታጣቂዎች የጦር መሳሪያ ታቀርባለች በሚል ትወቅሳለች።
ቴህራንም ሃማስን ጨምሮ ለሌሎች የፍልስጤም ታጣቂዎች ድጋፍ አላደርግም በሚል ክሱን አታስተባብልም።
የእስራኤል ጦር ባለፈው ወር ወደ ዌስትባንክ ሊገባ የነበረ ጸረ ታንክ እና ሌሎች ተተኳሾችን በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን መግለጹን ሬውተርስ አስታውሷል።
ከስድስት ወር በፊት የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በዌስትባንክ ከ450 በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል፤ ከ4 ሺህ 600 በላዩም ቆስለዋል።
እስራኤል በ1967ቱ የስድስት ቀናት ጦርነት በተቆጣጠረችው ዌስትባንክ ከ800 ሄክታር በላይ መሬት በመንጠቅ ለሰፈራ ቤቶችና የንግድ ህንጻዎች መገንቢያ መከለሏን በቅርቡ ይፋ ማድረጓ ይታወሳል።
በዌስትባንክና ፍልስጤማውያን ነጻ ሀገር ስንመሰርት መዲናችን ትሆናለች ባሏት ምስራቅ እየሩሳሌም ከ3 ሺህ 600 በላይ የሰፈራ ቤቶችን ለመገንባት የቀረበ እቅድም ጸድቋል።
ከፊል ዌስትባንክን የሚያስተዳድረው የሙሀመድ አባስ ፋታህ ፓርቲ ስለሰፈራ ቤቶቹ ግንባታም ሆነ እስራኤል ስለጠቀለለችው መሬት በመግለጫው አላነሳም።
አለማቀፍ እውቅና ያለው የፍልስጤም አስተዳደር በእስራኤልም እምብዛም አይነቀፍም።
ፓርቲው ከእስራኤል ጋር ያለውን ልዩነት በድርድር መፍታት የተሻለ አማራጭ ነው ብሎ ያምናል።
በአንጻሩ ከ2007 ጀምሮ ጋዛ ሰርጥን የሚያስተዳድረው ሃማስ የትጥቅ ትግልን መርጧል።
የፍልስጤም ነጻ ሀገር ምስረታ አንድ የሚያደርጋቸው ፋታህ እና ሃማስ በስልጣን ሽኩቻ በጋዛ ግጭት ውስጥ መግባታቸው የሚታወስ ሲሆን የ10 አመት ቅራኔያቸውን ለመፍታት መስማማታቸው ይታወሳል።
የፍልስጤሙ ፕሬዝዳንት ሙሀመድ አባስ የተለሳለሰ አቋም ቴል አቪቭ በዌስትባንክ የሰፈራ ፕሮግራሟን እንድትገፋበት መንገድ ጠርጓል በሚል የሚተቹ አሉ።