ለሶስተኛ ዙር የተመረጡት ፕሬዝዳንቱ በሆንግ ኮንግ መረጋጋት እንዲኖር ታይዋንን ደግሞ ለውህደት እንድትዘጋጅ አሳስበዋል
ፕሬዝዳንት ዢ ዘመናዊ ወታደራዊ ተቋም ግንባታ ላይ እንደሚያተኩሩ ገለጹ።
በዓመታዊው የቻይና የፓርላማ ስብሰባ ላይ የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ደህንነትን ማጎልበት ላይ እንደሚያተኩር አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ቻይና ደህንነቷን ማጎልበት አለባት፤ "ትልቅ የብረት ግንብ" ለመፍጠር መከላከያን ማዘመን አለባት ብለዋል።
ሦስተኛ የስልጣን ዘመናቸውን የጀመሩት ዢ፤ በዓመታዊው የፓርላማ ስብሰባ መዝጊያ ላይ ንግግር ሲያደርጉ ነው ይህን ያሉት።
"ደህንነት የእድገት መሰረት ሲሆን መረጋጋት የብልጽግና ቅድመ ሁኔታ ነው። የሀገር መከላከያንና የመከላከያ ሰራዊትን ሙሉ በሙሉ ማዘመን አለብን። የሀገር ሉዓላዊነትና ደህንነትን በብቃት የሚጠብቅ ታላቅ የብረት ግንብ መገንባት አለብን" ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ዢ "ታማኝ" አጋሮቻቸውን በከፍተኛ የደህንነት ቦታዎች ላይ መሾማቸው ተነግሯል።
የቻይናው ፕሬዝደንት አክለውም ሀገሪቱ በሳይንስ እና በቴክኖሎጂ ዘርፍ ራሷን መቻልና ጥንካሬ ማግኘት አለባት ብለዋል።
ዶቼዌሌ እንደዘገበው አሜሪካ ቻይና ቺፕ ማምረቻ መሳሪያዎችን እንዳታገኝ ከልክላለች።
ፕሬዝዳንት ዢ በሆንግ ኮንግ መረጋጋት እና ቤጂንግ የግዛቷ አካል አድርጋ ከምትመለከታት ከታይዋን ጋር ውህደትን ጠይቀዋል።
"የቻይና ህዝብ ታላቅ ተኸድሶ ወደማይቀለበስ ታሪካዊ ሂደት ውስጥ ገብቷል" ብለዋልም።
ቤጂንግ ባለፈው ሳምንት ከፍተኛ የደህንነት በጀት በጅታለች።