ሺ ጅንፒንግ ቻይናን በፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ ለሶስተኛ ጊዜ ተመረጡ
ሶስት ሺህ አባላት ያለው የቻይና ህግ አውጪ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሺ ጅንፒንግን ለሶስተኛ ጊዜ መርጧል
ፕሬዝዳንት ጂንፒንግ በቻይና ታሪክ ከሀገሪቱ መስራች ማኦ ዜዶንግ በኋላ በለስልጣን ላይ ረጅም ዓመት የቆዩ መሪ ተብለዋል
ጂንፒንግ ቻይናን በፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ ለሶስተኛ ጊዜ ተመረጡ።
የዓለማችን ሁለተኛዋ ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤቷ ቻይና በስልጣን ላይ ያሉት ሺ ጂንፒንግን ለሶስተኛ ዙር ፕሬዝዳንት አድርጋ መርጣለች።
ሶስት ሺህ አባላት ያሉት የቻይና ህግ አውጪ ምክር ቤት ባካሄደው ጉባኤ ፕሬዝዳንት ዥንፒንግ ለተጨማሪ ሶስተኛ ዙር በስልጣን እንዲቀጥሉ ወስነዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
የ69 ዓመቱ ሺ ጂንፒንግ ከፈረንጆቹ 2012 ጀምሮ ቻይናን በፕሬዝዳንትነት እየመሩ የቆዩ ሲሆን በፕሬዝዳንትነት ለሶስተኛ ዙር እንዲቀጥሉ መመረጣቸው በታሪክ የቻይና ተጽዕኖ ፈጣሪ መሪ ያደርጋቸዋል ተብሏል።
የቻይናው ኮሚኒስት ፓርቲ ባሳለፍነው ህዳር ባካሄደው ጉባኤ ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ የፓርቲው ሊቀመንበር አድርጎ መምረጡ ይታወሳል።
ፕሬዝዳንቱ ሀገራቸው በተለይም በታይዋን ጉዳይ እና በሌሎች ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ከአሜሪካ እና አውሮፓዊያን ጋር የገቡበት የንግድ ጦርነት ዋነኛ ፈተናቸው ይሆናል ተብሏል።
ቻይና በታሪኳ ከሌሎች ሀገራት ጋር ወደ ይፋዊ ጦርነት አለመግባቷ ለእድገቷ ዋነኛ ምንጭ እንደሆነ ይነገራል።
ከዚህ በፊት ቻይና በተለይም በሁለቱም የዓለም ጦርነቶች እና በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት በይፋ ወደ ጦርነት በተባበሩት መንግታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት አስችሏታል።
ቻይና የዓለምን ኢኮኖሚ ለመቆጣጠር እየሰራች ነው በሚል እና በዩክሬን ጦርነት ጉዳይ ሩሲያን ትደግፋለች የሚል ወቀሳ እየቀረበባት ሲሆን አሜሪካ እና ምዕራባዊያን ለቤጂንግ ጎረቤት በሆኑ ሀገራት ወታደራዊ ማዘዣዎችን ለማቋቋም በእንቅስቃሴ ላይ መሆናቸው ለፕሬዝዳንት ሺ ፒንግ ትልቅ የቤት ስራ እንደሚሆንባቸው ይጠበቃል።
ፕሬዝደንት ሺ ጅንፒንግ በነገው ዕለት ለሀገሪቱ ዜጎች ንግግር እንደሚያደርጉ የሚጠበቅ ሲሆን አዲስ የካቢኔ አባላቸውንም ይፋ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።