በቻይና የተቀሰቀሰው አዲስ ወረርሽኝ ምንድን ነው?
የአለም ጤና ድርጅት በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ይደረጉ የነበሩ የጥንቃቄ እርምጃዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ አሳስቧል
ህጻናትን በስፋት እያጠቃ ያለው የሳንባ ምች መሳይ በሽታ ዙሪያ ቤጂንግ ግልጽ መረጃ እንድትሰጥ እየተጠየቀች ነው
በቻይና መዲና ቤጂንግ እና ላዮኒንግ በተሰኘችው ግዛት የተቀሰቀሰው አዲስ ወረርሽኝ አሳሳቢ ሆኗል።
ህጻናትን የሚያጠቃው “የሳንባ ምች መሰል ወረርሽኝ” ሆስፒታሎችን ማጨናነቅ ከጀመረ ዋል አደር ብሏል።
ከቤጂንግ በ804 ኪሎሜትሮች ርቃ በምትገኘው ላዮኒንግ ትምህርት ቤቶች ለመዘጋት ተቃርበዋልም ነው የተባለው።
ምንነቱ እስካሁን ባልተለየው በሽታ የተያዙ ህጻናት ከፍተኛ ትኩሳት ቢኖራቸውም የጉንፋን ምልክት አልታየባቸውም፤ ከመተንፈሻ አካላት ጋር የተያያዙ በሽታዎች ምልክቶችም የላቸውም ተብሏል።
የኮቪድ 19 ቫይረስ በውሃን እንደተከሰተ የቻይና ብሎም የአለም ስጋት ይሆናል የሚል ስጋቱን አስቀድሞ የገለጸው “ፕሮሜድ” የተሰኘው የበሽታ ቅኝት ስርአት አዲሱን የቻይና ወረርሽኝ በስጋትነት ጠቅሶታል።
የአለም ጤና ድርጅትም በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ይደረጉ የነበሩ ጥንቃቄዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ አሳስቧል።
የፊት መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ፣ የህመሙ ምልክት ካለባቸው ሰዎች መራቅ እና የታመሙ ሰዎችም ከቤታቸው እንዳይወጡ የሚል ማሳሰቢያውንም በድረገጹ ላይ አስፍሯል።
ሰዎች ከሚሰበሰቡባቸው ስፍራዎች እንዲርቁና ከቻሉ ከቤታቸው እንዳይወጡም ነው ያሳሰበው።
“ማይኮፕላዝማ ኒሞኒያ” በተሰኘው ባክቴሪያ ምክንያት ሊከሰት እንደሚችል የተገመተው አዲሱ በሽታ ሳንባን ክፉኛ እንደሚጎዳ ተገልጿል።
“ፕሮሜድ” ህጻናትን እያጠቃ ያለው “የሳንባ ምች መሳይ በሽታ” መቼ መስፋፋት ጀምሮ ወደ ወረርሽኝነት እንደሚለወጥ ባይገልጽም ህጻናትን በፍጥነት ማዳረሱ አሳሳቢ ሆኗል።
የአለም ጤና ድርጅትም ቻይና የበሽተኞቹን መረጃ፣ የስርጭት መጠኑን እንዲሁም በሆስፒታሎች ላይ የፈጠረውን ጫና በተመለከተ ዝርዝር መረጃ እንድታጋራው ጠይቋል።
ቤጂንግ በፈረንጆቹ 2003 የተቀሰቀሰውን የሳርስ ወረርሽኝ እና በ2019 የተከሰተውን የኮሮና ወረርሽኝ በተመለከተ ግልጽ መረጃ በመስጠት ረገድ ክፍተት አለባት የሚሉ ትችቶች ሲሰነዘሩባት መቆየቱ የሚታወስ ነው።
በቤጂንግ እና ላዮኒንግ የተቀሰቀሰው በሽታ ህጻናትን ብቻ ማጥቃቱና እስካሁን ህይወት ስለመቅጠፉ አለመዘገቡ እንደ ኮቪድ የአለም ስጋት የመሆን እድሉን ቢያሳንሰውም ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ባለሙያዎች ማሳሰባቸውን ዴይሊሜል ዘግቧል።