የዓለም ጤና ድርጅት ኮቪድ-19 ዓለም ድንገተኛ የጤና አደጋ መሆኑ አብቅቷል አለ
7 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን የገደለውን ቫይረስ ሀገራት ከሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ጋር መቆጣጠር ይችላሉ ተብሏል
ሆኖም ኮቪድ ዓለም አቀፍ የጤና ስጋትነት እንዳላበቃ የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል
የዓለም ጤና ድርጅት ኮቪድ-19 ከ3 ዓመታት በኋላ የድንገተኛ የጤና ቀውስ መሆኑ አብቅቷል ብሏል።
ድርጅቱ ሀገራት ከ6.9 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን የገደለውን ቫይረስ ከሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ጋር መቆጣጠር አለባቸው ሲል አስታውቋል።
ኮቪድ-19 ከፍተኛው የማስጠንቀቂያ ደረጃ የሆነው "ዓለም አቀፍ አሳሳቢ የህዝብ ጤና ድንገተኛ አደጋ" በመባል ከጥር 30፤ 2020 ጀምሮ ታውጇል።
የዓለም ጤና ኤጀንሲ የድንገተኛ አደጋ ኮሚቴ ሀሙስ ዕለት ተገናኝቶ ድርጅቱ የኮሮና ቫይረስ ቀውስን ማብቃቱን እንዲያውጅ ምክረ-ሀሳብ ሰጥቷል።
"ኮቪድ-19ን ዓለም አቀፍ የጤና ድንገተኛ አደጋ ማብቃቱን ሳውጅ በታላቅ ተስፋ ነው" ያሉት የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም፤ የአደጋ ጊዜ ማብቂያው ኮቪድ ዓለም አቀፍ የጤና ስጋትነት አብቅቷል ማለት አይደለም ሲሉም አክለዋል።
ሮይተርስ እንደዘገበው በመግለጫው ወቅት የዓለም ጤና ድርጅት አባላት ወረርሽኙ በተከሰተበት ወቅት ሀገራት የቀሰሙትን ትምህርት እንዲያሰላስሉ አሳስበዋል።
ኮቪድ-19 በጥር፤ 2021 ከ100 ሽህ በላይ ሰዎች ከነበረው ሳምንታዊ ከፍተኛ የሞት ምጣኔ እስከ ሚያዝያ 24፤ 2023 ድረስ ወደ ሦስት ሽህ 500 ቀንሷል ሲል የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ጠቅሷል።
ለዚህም ሰፊ ክትባት፣የተሻሉ ህክምናዎችን እና በሽታ የመከላከል አቅም ከፍ ማለት ምክንያት ነው ተብሏል።