ለኮቪድ 19 ክትባት እንዲገኝ መሰረት የሆኑት ተመራማሪዎች የኖቬል ሽልማት አሸነፉ
ፕሮፌሰር ካታሊን ካሪኮ እና ድሪው ዌስማን በህክምና ዘርፍ የዘንድሮው የኖቬል ሽልማት አሸናፊ መሆናቸው ተነግሯቸዋል
ተመራማሪዎቹ የቀደመውን የክትባት አመራረት የለወጠ ቴክኖሎጂን አስተዋውቀዋል
በመጋቢት ወር 2020 የተቀሰቀሰው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በመላው አለም ከ6 ነጥብ 9 ሚሊየን በላይ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል።
በአሁኑ ወቅትም ከ696 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን የወርልዶ ሜትር መረጃ ያሳያል።
ከ70 በመቶ በላይ የአለማችን ህዝብ ቢያንስ አንዴ የኮቪድ 19 ክትባትን መውሰዱንም የአለም ጤና ድርጅት ይገልጻል።
የዘንድሮው የኖቬል ሽልማትም ባለፉት ሶስት አመታት የምድራችን ፈተና ለሆነው የኮሮና ወረርሽኝ መፍትሄ የሚሆን ቴክኖሎጂን ያስተዋወቁ ተመራማሪዎችን እውቅና ሰጥቷል።
በህክምናው ዘርፍ ለአለም ትልቅ ፋይዳ ያለው ምርምር ያደረጉት ፕሮፌሰር ካታሊን ካሪኮ እና ፕሮፌሰር ድሪው ዌስማን የኖቬል ሽልማትን በጋራ ይወስዳሉ ብሏል የኖቬል ሽልማት ኮሚቴ።
ተመራማሪዎቹን የኖቬል ተሸላሚ ያደረገው “ኤምአርኤንኤ” ምንድን ነው?
ከኮቪድ በፊት ለተከሰቱ ወረርሽኞች የሚዘጋጁ ክትባቶች እየተሰራጨ የሚገኘውን ቫይረስ ወይም ባክቴሪያ በማዳከምና ወደ ሰውነት እንዲገባ በማድረግ ላይ የተመሰረተ ቴክኖሎጂን የሚጠቀሙ ናቸው።
በአንጻሩ የኖቬል ተሸላሚዎቹ ያስተዋወቁት “ሜሴንጀር ሪቦኑክሊክ አሲድ (ኤምአርኤንኤ)” ቴክኖሎጂ ከኮሮና ቫይረስ ፕሮቲን ማምረት የሚያስችል ነው።
እንደ ሞደርና እና ባዮንቴክ (ፋይዘር) ያሉ ኩባንያዎችም ይህንኑ አዲስ መንገድ በመከተል ክትባቶችን በማምረት ለሚሊየኖች ደርሰዋል ይላል የሬውተርስ ዘገባ።
በ“ኤምአርኤንኤ” ቴክኖሎጂ የሚመረቱ ክትባቶች ወደ ሰውነታችን ሲገቡ ህዋሳቶቻችን የኮሮና ቫይረስን የሚያዳክም ፕሮቲን በብዛት ማምረት ይጀምራሉ።
ተመራማሪዎቹ ከ1990ዎቹ ጀምሮ በአሜሪካ ሲያጠኑት ቆይተው የኮሮና ወረርሽኝ ሲከሰት በስፋት የተሞከረውና ውጤታማነቱ የተረጋገጠው አዲስ የክትባት አመራረት ስልት እንደ ካንሰር ላሉ በሽታዎች ክትባት ለመፈለግ መሰረት መሆኑም ተነግሯል።