ፖለቲካ
የቻይና ይፋ ያደረገችው አዲስ ብሄራዊ ካርታ ጎረቤቶቿን ለምን አስቆጣ?
የደቡብ ቻይና ባህር ወደ ቻይና የጠቀለለውን ካርታ ቤጂንግ የተለመደና በህግ የተፈቀደ ነው ብላለች
ህንድ፣ ማሌዥያ እና ፊሊፒንስ ካርታውን የተቃወሙ ሲሆን፤ ሩሲያ በዝምታ መመልከቷ ተነግሯል
ቻይና ይፋ ያደረገችው አዲስ ብሄራዊ ካርታ ጎረቤት ሀገራትን አስቆጥቷል።
ፊሊፒንስ ከህንድና ማሌዥያ በመቀጠል በቻይና አዲስ ካርታ ጠንካራ አቋማን ያሳወቀች ሀገር ሆናለች። ሀገሪቱ ቤጂንግ ግዛቴን በይገባኛል ወስዳብኛለች ስትል ወንጅላለች።
ቻይና ድንበሮቿን በተሳሳተ መንገድ ይገልጻል ያለችውን ብሄራዊ ካርታ አስተካክላ ሰኞ ዕለት ይፋ አድርጋለች።
ሀገሪቱ "ችግር ያለባቸው ካርታዎች" በማለት የምትጠራውን አካበቢ ለማስተካከል ከፈረንጆቹ 2006 ጀምሮ በመደበኛነት ስታስተካክል መቆየቷን ተናግራለች።
ካርታው ውዝግብ ያለበትን የደቡብ ቻይና ባህር መጠቅለሉን ፊሊፒንስ "አልቀበለውም" ብላለች።
ህንድ በካርታው ላይ ቅራኔዋን ያሳየች የመጀመሪያዋ ሀገር ስትሆን፤ ግዛቶቼ ተወስደው በቻይና ተጠቅልለውብኛል ስትል ከሳለች።
የማሌዥያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴርም ካርታውን ውድቅ በማድረግ፤ ሉዓላዊነቱን አሳልፎ እንደማይሰጥ ገልጿል።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ዋንግ ዉቤን ቅሬታውን አጣጥለው፤ ማሻሻያው የተለመደና በህግ የተፈቀደ ነው ብለዋል።
ካርታውን ከሚገባው በላይ መተንተን አያስፈልግም ሲሉም አክለዋል።