የባይደን አስተዳደርም በቤጂንግ የቴክኖሎጂ ዘርፍ ላይ ማዕቀቦችን መጣሉን ገፍቶበታል
የአሜሪካ እና ቻይና የሃያልነት ፍልሚያ በቴክኖሎጂው ዘርፍም በጉልህ ይታያል።
አሜሪካ የብሄራዊ ደህንነቴ ስጋር ናቸው ያለቻቸውን የቻይና የቴክኖሎጂ ውጤቶች ወደ ሀገሪቱ እንዳይገቡ መወሰኗን ተከትሎ ቤጂንግ አጻፋውን መልሳለች።
ለተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ምርት ወሳኝ ግብአት የሆኑ ሁለት የብረት ማዕድናት ከቻይና ውጭ ለአለም ገበያ እንዳይቀርቡ መመሪያ በማውጣት።
ቤጂንግ ለውጭ ገበያ አይቀርቡም ያለቻቸው ጋሊየም እና ጀርማኒየም የተባሉ ማዕድናትን ነው።
ማዕድናቱ ከኤሌክትሮኒስክ ተሽከርካሪዎች እስከ ስማርት ስልኮች ከሶላር ፓኔሎች እስከ ጦር መሳሪያዎች ምርት ድረስ ወሳኝ ግብአት መሆናቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።
ቻይና ከአለማችን የጋሊየም ምርት 94 በመቶ፤ የጀርማኒየም ምርት ደግሞ 83 በመቶ ድርሻ ትይዛለች።
ከነሃሴ 1 2023 ጀምሮ ተግባራዊ የሆነው አዲስ መመሪያም የሰሚኮንዳክተር ኢንዱስትሪዎችን ክፉኛ ይጎዳል ተብሏል።
በተለይ ከጸሃይ ሃይል ኤሌክትሪክ ለማመንጨት የሚውሉ ሶላር ፓኔሎችን በስፋት ለማምረት እክል ሊፈጥር እንደሚችል የአውሮፓ ህብረት ስጋቱን ገልጿል።
የቤጂንግ እርምጃ ለዋሽንግተን ግልጽ መልዕክት የሰደደና ፖለቲካዊ ይዘቱ ይጎላል የሚሉ ባለሙያዎች የጋሊየም እና ጀርማኒየም አቅርቦት መቀነስ በኤሌክትሮኒክስ ገበያው ላይ ጉልህ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር እየተናገሩ ነው።
የባይደን አስተዳደርም የቴክኖሎጂ ጦርነቱን የሚያፋፍምና በቻይና የቴክኖሎጂ ሴክተር ላይ የሚያነጣጥር አዲስ እገዳ ለመጣል መዘጋጀቱን ብሉምበርግ አስነብቧል።