ቻይና እርምጃውን የወሰደችው አሜሪካ አንድ የቻይና ቆንስላ እንዲዘጋ ከወሰነች በኋላ ነው
ቻይና በቼንግዱ የሚገኘው የአሜሪካ ቆንስላ እንዲዘጋ ወሰነች
ቻይና ዉሳኔውን ያሳለፈችው ዩኤስ በሂዩስተን የሚገኘው የቻይና ቆንስላ ስራ እንዲያቆም ካደረገች ከቀናት በኋላ ነው፡፡ በቻይና ቼንግዱ የሚገኘው የአሜሪካ ቆንስላ ዲፕሎማቶች ከዛሬ ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ስራቸውን እንዲያቆሙ ትዕዛዝ መተላለፉን የቻይና ዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ያመለክታል፡፡
አሜሪካ በሂዩስተን የሚገኘውን የቻይና ቆንስላ በተናጥል ዉሳኔ መዝጋቷ ቻይና ለወሰደችው እርምጃ ምክንያት መሆኑም በመግለጫው ተካቷል፡፡ ሲኤንኤን እንደዘገበው ፣ የአሜሪካ የተናጥል ዉሳኔ ከፍተኛ የዓለም አቀፍ ህግ ጥሰት እንደሆነ እና መሰረታዊ የዓለም አቀፍ ግንኙነት መርሆችን የተላለፈ መሆኑንም ቻይና አስታውቃለች፡፡
አሜሪካ የሂዩስተኑን የቻይና ቆንስላ የዘጋችው ቻይና የአሜሪካ የሆኑ የአእምሮ ፈጠራ ዉጤቶችን እየሰረቀች በመሆኗ እንደሆነ የሀገሪቱ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ገልጸዋል፡፡ ከአሜሪካ ባለፈ የአውሮፓ የአእምሮ ፈጠራ ዉጤቶችም በቻይና እየተሰረቁ መሆናቸውን ፖምፒዮ ገልጸዋል፡፡
በደቡብ ምዕራብ ቻይና ሲቹዋን ግዛት ዋና ከተማ ቼንግዱ የሚገኘው የአሜሪካ ቆንስላ እንደ አውሮፓውያኑ በ1985 የተቋቋመ ሲሆን አሁን ላይ 200 ያህል ሰራተኞች አሉት፡፡ ቆንስላው የሚገኝበት ስፍራ የራስ ገዝ አስተዳደር በሆነችው ቲቤት አቅራቢያ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ያለው እንደሆነ ይገለጻል፡፡
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሀገሪቱ የሚገኙ ተጨማሪ የቻይና ቆንስላዎችን ሊዘጉ እንደሚችሉም ይፋ አድርገዋል፡፡
ከአሜሪካ ጋር በበርካታ ዘርፎች መገዳደር የምትችልበትን ጡንቻ ያዳበረችው ቻይናም አሜሪካ ለምትወስዳቸው እርምጃዎች ሁሉ አጸፋውን ለመመለስ ዝግጁ መሆኗን አስታውቃለች፡፡
በዓለማችን 2 ቀዳሚ የኢኮኖሚ ባለቤቶች በአሜሪካ እና በቻይና መካከል በተለያዩ መስኮች ዉጥረት በመንገስ ላይ ይገኛል፡፡
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር አንዴ በንግድ ሌላ ጊዜ በኮሮና ቫይረስ ቀጥሎም በሆንግ ኮንግ የደህንነት ህግ ጉዳይ ከቻይና ጋር በተደጋጋሚ መላተሙን ቀጥሏል፡፡