ቻይና አዲስ ባወጣችው ህግ ሆንግ ኮንግን ልታዳክም አስባ ይሆን?
ለ99 ዓመታት በሊዝ ውል ለብሪታኒያ ተሰጥታ የነበረቸው ሆንግ ኮንግ የውሉ ጊዜ ሲጠናቀቅ በአውሮፓውያኑ 1997 ወደ ቻይና ተቀላቀለች
በሆንግ ኮንግ ጉዳይ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ይከላከላል የተባለው አዲሱ የቻይና ህግ ክርክር አስነስቷል
በሆንግ ኮንግ ጉዳይ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ይከላከላል የተባለው አዲሱ የቻይና ህግ ክርክር አስነስቷል
ከሰሞኑ ቤጅንግ የሆንግ ኮንግን ጉዳይ የተመለከተ ሕግ ማዘጋጀቷን በተመለከተ ከፍተኛ ክርክር ሲነሳ ቆይቷል፡፡ በአንድ ሀገር ሁለት ሥርዓት ውስጥ ያለችው ሆንግ ኮንግ ከሌሎች የቻይና ግዛቶች የተለየ ነጻነትና አስተዳደር አላት፡፡
ለ99 ዓመታት በሊዝ ውል ለብሪታኒያ ተሰጥታ የነበረቸው ሆንግ ኮንግ የውሉ ጊዜ ሲጠናቀቅ በአውሮፓውያኑ 1997 ወደ ቻይና ተቀላቀለች፡፡ በወቅቱ ወደ ቻይና ስትመለስ ልዩ አስተዳደር ክልል ሆና ነበር፡፡
በዚህም መሰረት አንድ ሀገር ሁለት ሥርዓቶች (ዋን ካንትሪቱ ሲስተም) በሚል ቤጅንግና ሆንግ ኮንግ ቀጠሉ፡፡ የተለየችው ግዛት ሆንግ ኮንግ የራሷ ሕግ አውጭ፣ሕግ አስፈጻሚና ሕግ ተርጓሚ አላት፡፡ ይሁንና የራሷ ወታደራዊ ተቋምና በመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት ተወካይ የላትም፡፡ ከዚያ በመለስ ግን የተለየ ነጻነት አላት፡፡
ግዛቲቱ ታዲያ በርካት የጸጥታ ችግሮች ሲስተዋሉበት እንደነበር የቤጅንግ ሰዎች ያሳሉ፡፡ ይህንን ተከትሎም አሁን ላይ ለግዛቲቱ አዲስ የጸጥታ ሕግ መውጣቱን ነው ሀገሪቱ ያስታወቀችው፡፡
ሕጉ ሆንግ ኮንግን ከቻይና ስለመገንጠል፣ ሀገር ክህደትንና ሽብርተኝነትን ለመከላከልና ለማውገዝ ያለመ ነው ተብሏል፡፡ከዚህ ባለፈም በሆንግ ኮንግ ጉዳይ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመመከትም ያለመ ነው ተብሏል፡፡
የንብረት፣የኮንትራት፣የግለሰብ መብቶችን፣ጋብቻና ቤተሰብ፣ውርስና የፍትሐ ብሔር ተጠያቂነትን የሚመለከቱ ጉዳዮችን የያዘው ይህ አዲ የጸጥታ ሕግ ታዲያ ከአሜሪካ በኩል ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡
ዋሸንግተን ጉዳዩን ኒወዮርኩ ተቋም ለመውሰድ በማሰብ አጀንዳ እንዲያዝላት ጠይቃለች፡፡ በዚህም መሰረት የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የሆንግ ኮንግን የጸጥታ ሕግ በተመለከተ አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራና አጀንዳ እንዲያዝላት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ማይክ ፖምፒዮ በኩል ጠይቃለች፡፡
በቻይና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አምባሳደር ዙሃንግ ጁን አሜሪካ ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ለመውሰድ ያቀረበችው ጥያቄ መሰረት የሌለው ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ ዲፕሎማቱ በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጹሑፍ የሆንግ ኮንግ ጉዳይ የሀገር ቤት ጉዳይ በመሆኑ የጸጥታው ምክር ቤት ሥራ እንዳልሆነ አስታውቀዋል፡፡
ሩሲያም ከቻይና ጎን በመቆም የአሜሪካን ጉዳዩን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይመልከተው የሚለውን ጉዳይ ተቃውማለች፡፡ ከሞስኮ የመጣው መግለጫ የሆንግ ኮንግ ጉዳይ የቻይና ውስጥ ጉዳይ በመሆኑ ወደ ጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ሊወሰድ እንደማይገባ ያመለክታል ነው የተባለው፡፡
የቻይናው ተንታኝ ዊሊ ላም እንደሚለው አዲሱ ሕግ የሆንግ ኮንግ ሰዎች ቻይናን እንዳይቃወሙ ሊያደረግ ይችላል የሚል ፍርሀት እንዳለ ያነሳል፡፡በነጻነት የመናገርንና የማመጽ መብትን ከመጋፋቱም ባለፈ እንደ ክህደት ተደርጎ ሊቆጠር እንደሚችልም ባለሙያው ያነሳል፡፡
ሌሎች የዴሞክራሲ አቀንቃኞችም ሆንግ ኮንግ ያሏት ተቋማት በቻይና ይዋጣሉ፣መቃወምና ሌሎች የዴሞክራሲ መብቶች ጉዳይ አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል የሚሉ ስጋቶችን ስለማንሳታቸው ይገለጻል፡፡ የሆንግ ኮንግ የፍትሕ አካልም ልክ ቤጅንግ እንዳለው ሊሆን እንደሚችል ፣በአጠቃላይ ቤጅንግ በሆንግ ኮንግ የራሷን ሙሉ ቁጥጥር ልታደርግ ነው የሚሉ አሉ፡፡
ቻይና ግን በልዩ አስተዳደሯ ሆንግ ኮንግ የሕግ የበላይነት አደጋ ላይ እንዳይወድቅ፣ሉዓላዊነት እንዳይነካ፣አንድ ሀገር ሁለት ሥርዓት የሚለውን የቤጅንግና የሆንግ ኮንግን የቆየ ውል እንዳይሸራረፍ፣ብሔራዊ ጽጥታና ጥቅሞችን ለማስከበር የወጣ ሕግ ነው ብላለች፡፡ ባለፈው ዓመት ጀምሮ የተቀሰቀሰው አመጽም ለዚህ ሕግ መውጣት መነሻ ስለመሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ባለፈው አርብ ለምክር ቤቱ የተላው እና ከሰሞኑ እንደተዘጋጀ የተነገረው ይህ የሆንግ ኮንግ የጸጥታ ሕግ በቻይና ምክር ቤት በአብላጫ ድምጽ ጸድቆዳ በላይ አካላት ተልኳል፡፡ ሆንግ በቻይና ውስጥ የምትገኝ ሲሆን ከሌሎች የቻይና ግዛቶች በተለየ የራሷ የፍትሕ ፣የጸጥታ እንዲሁም ሌሎች ሕጎች አሏት፡፡