ፕሬዝዳንት ትራምፕ የተቃውሞ ሰልፎችን ለመቆጣጠር የጦር ሰራዊት ለማሰማራት ዛቱ
የአፍሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንቶች የፍሎይንድ ግድያ ያወገዙ ሲሆን በብዙ ሀገራትም ሰልፎች እየተካሄዱ ነው
ትራምፕ የጦር ሰራዊት ለማሰማራት ቢዝቱም በአሜሪካ የተጀመሩ ሰልፎች ተባብሰው ቀጥለዋል
ፕሬዝዳንት ትራምፕ የተቃውሞ ሰልፎችን ለመቆጣጠር የጦር ሰራዊት ለማሰማራት ዛቱ
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በፖሊስ በተገደለው ጆርጅ ፍሎይድ ምክንያት ምክንያት በአሜሪካ እየተባባሰ የመጣውን አመፅ ለማስቆም የጦር ሰራዊት ለማሰማራት ዝተዋል፡፡
ከተሞች እና ስቴቶች የተቃውሞ ሰልፉን መቆጣጠር ከተሳናቸው እና “ነዋሪዎቻቸውን መከላከል” ካልቻሉነ ሠራዊቱን በማሰማራት “ለችግሩ በፍጥነት መፍትሄ ይሰጣል” ብለዋል፡፡
በጆርጅ ፍሎይድ ሞት ምክንያት የተጀመሩ የተቃውሞ ሰልፎች ሰባተኛ ቀናቸው ደፍነዋል፡፡
ትራምፕ በዋይት ሀውስ ንግግር ሲያደርጉ ፖሊሶች በአቅራቢያው ካለው መናፈሻ በአስለቃሽ ጋዝ እና የጎማ ጥይት ሰልፈኞችን ሲበትኑ ነበር፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከንግግራቸው በኋላ መናፈሻውን አቋርጠው ጉዳት የደረሰበት ቤተ ክርስቲያን አጠገብ በመቆም ፎቶግራፍ መነሳታቸውን ተከትሎ፣ ለራሳቸው ፎቶ የመነሳት እድል ለመፍጠር በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የኃይል እርምጃ እንዲወሰድ አድርገዋል በሚል ትችት ተሰንዝሮባቸዋል፡፡
በዋይት ሀውስ የጦር ሠራዊት አባላት መግባታቸውንም ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ የተቃውሞ ሰልፎች እና አመጾች አሁንም የቀጠሉ ሲሆን በቺካጎ 2 ሰዎች ሲገደሉ በሴንት ሉዊስ ሚዝሪ 4 ፖሊሶች በጥይት ተመተው ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል ገብተዋል፡፡
የአፍሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንቶች የፍሎይንድ ግድያ አውግዘዋል
የቀድሞ ርዕሰ ብሔራት እና ርዕሰ መንግስታት መድረክ የአፍሪካ ሀገራት ለተፈጸመው ግድያ “ጠንካራ ተቃውሞ ሊያሰሙ” እንደሚገባ እና “የዚህ ወንጀል ፈጻሚዎች እና ሌሎች የዚህን ዓይነት ወንጀሎች ሁሉ ጠንካራ እርምጃ እንዲወሰድባቸው” ጥሪ እንዲያቀርቡ በቀድሞው የቤኒን ፕሬዚዳንት ኒሲፎር ሱግሉ አማካኝነት ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
“ማንም ምንም አይነት የጭካኔ ደረጃ ላይ ቢደርስ በስተመጨረሻ መላው ዓለም ከእንቅልፉ ነቅቶ ጭቆናና ጭካኔን በቃችሁ ማለት ጀምሯል፡፡ አውሮፓዊ ም ይሁን ፣ አረብ ፣ እስራኤል ፣ ህንድ ፣ ቻይናዊ ፣ ጃፓናዊ ፣ አርጀንቲናዊ ፣ ወዘተ በቃ ማለት በቃ ነው” ብለዋል የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኒሲፎር ሱግሉ ፡፡
የጋና ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ-አዶ በትዊተር ገፃቸው ጥቁር ሰዎች “ተደናግጠዋል ተጎድተዋልም” ብለዋል ፡፡
የደቡብ አፍሪካው ገዢ ፓርቲ ፣ የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኤኤንሲ) ፣ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ “የዘር ግጭትን ለመከላከል እና ከተለያዩ ዘሮች ጋር ማህበራዊ ትስስር ለመፍጠር” ከአሜሪካ ጋር እንዲቆሙ አሳስቧል ፡፡
በተለያዩ የዓለም ክፍሎችም ግድያውን በመቃወም ሰልፎች በመካሄድ ላይ ናቸው
ከአምስተርዳም እስከ ሪዮ ዲ ጄኔሮ ድረስ በዓለም ዙሪያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ምክንያት ተቃውሞአቸውን ለማሰማት አደባባይ ወጥተዋል፡፡
በአምስተርዳም 3000 ያህል ሰዎች በፖሊስ የጭካኔ ተግባር እና የዘር ልዩነት ላይ የተቃውሞ ድምጻቸውን ለማሰማት ሰኞ ዕለት በከተማዋ ዳም አደባባይ ተሰብስበዋል፡፡
በሪዮ ዴ ጄኔሮ በሀገሪቱ ቤተ መንግሥት ፊት ለፊት ተገኝተው ድምጻቸውን ያስሰሙ የተቃውሞ ሰልፈኞች “ዘረኝነት ዓለም አቀፍ ከሆነ ፣ ፀረ-ዘረኝነትም እንዲሁ ነው” “እኛን መግደል ይቁም” እና “ፍትህ ዕውር አይደለም” የሚል መፈክር አስተጋብተዋል፡፡
በፈረንሳይ ፓሪስ ደግሞ ሰኞ ዕለት በአሜሪካ ኤምባሲ አቅራቢያ የተሰበሰቡ በርካታ የፈረንሳይ ፀረ-ዘረኝነት ድርጅቶችን የሚወክሉ ሰዎች የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል፡፡
በአሜሪካ የሚደረጉ ሰልፎችን በመደገፍ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተጣለውን ከቤት ያለመውጣት ህግ በመጣስ በርካታ ሰዎች በለንደን ለተቃውሞ ሰልፍ የወጡ ሲሆን ህጉን በመጣሳቸው ፖሊስ ብዙዎችን አስሯል፡፡
አውስትራሊያ ፣ በጀርመን ፣ በአየርላንድ ፣ በግሪክ እና በሌሎች በርካታ ሀገራት ላይም የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል ፤ በእቅድም ደረጃ የተያዘባቸው ሀገራት አሉ፡፡
ሰልፈኞች በለንደን
የዓለም መሪዎችም በጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ስሜታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡ የኒውዚላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርደርን በጆርጅ ፍሎይድ ሞት “በጣም መደንገጣቸውን” እንዲሁም በሀገራቸው የተካሄደውን የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚደግፉ ተናግረዋል፡፡
የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ በበኩላቸው በጥቁር ሰዎች ላይ የሚፈጸም የዘረኝነት ጥቃት “በአሜሪካም በካናዳም አለ” ብለዋል፡፡
ኮሮና ቫይረስ ክፉኛ በጎዳት ሀገረ አሜሪካ የተቀጣጠለው የተቃውሞ ሰልፍ ለሀገሪቱ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖባታል፡፡ እስካሁን ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ዜጎቿ በኮሮና ቫይረስ የተያዙባት አሜሪካ ከ106 ሺ በላይ ሞት አስተናግዳለች፡፡
ምንጭ፡- ሲኤንኤን