ቻይና በ2023 ከ200 በላይ በህዋ ቅኝት የሚያደርጉ መንኮራኩሮችን ልታሰማራ ነው
መንኮራኩሮቹ ከ60 በላይ የጠፈር ተልዕኮዎችን በመፈጸም እንደምትልክም ነው ያስታወቀችው
ቤጂንግ በ2023 በህዋ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የምትከውናቸውን ስራዎች የተመለከተው እቅድ ይፋ ሆኗል
ቻይና የፈረንጆቹ 2023 በህዋ ላይ ተጽዕኖዋን ከፍ የሚያደርጉ ስራዎችን እንደምትከውን አስታውቃለች።
በያዝነው አመት ከ200 በላይ በህዋ ቅኝት የሚያደርጉ የተለያዩ መንኮራኩሮችን እንደምታሰማራ ነው የ2023 የዘርፉ እቅዷ ያመላከተው።
በህዋ ላይ ቅኝት የሚያደርጉት መሳሪያዎች የኮሙዩኒኬሽን፣ የመሬት ቅኝት እና የአየር ንብረት ጥቆማን ወደ መሬት የሚልኩ ናቸው።
መሳሪያዎቹን ወደ ጠፈር ለመላክም ከ60 በላይ የጠፈር ተልዕኮዎችን እንደምትፈጽም የሀገሪቱ የስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ አካዳሚ ይፋ አድርጓል።
ይህም የቤጂንግን የህዋ ምርምር እና ቅኝት በእጅጉ እንደሚያሳድገው የአካዳሚው ምክትል ዳይሬክተር ጉ ሚንግኩን ለሲ ጂ ቲ ኤን ተናግረዋል።
ቲያንዡ 6፣ ሸንዙ 16 እና ሸንዙ 17 የተሰኙት የጠፈር ተልዕኮዎችም መሳሪያዎቹን ለማድረስ ከመሬት ወደ ጠፈር ይወነጨፋሉ ብለዋል።
በዚሁ አመት ዘመኑን የዋጁ የንግድ የሪሞት ሴንሲንግ ሳተላይቶችን ወደ ጠፈር የመላኩ ስራም ትኩረት እንደሚደረግበት ነው እቅዱ የሚያሳየው።
በጨረቃ እና ማርስ ላይም አዳዲስ የቅኝት መሳሪያዎችን በመትከል ምርምሯን እንደምትገፋበት የሀገሪቱ የስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ይፋ አድርጓል።
ሎንግ ማርች 6ሲ የተሰኘች ሮኬትን የማምጠቅ እቅድም ትናንት በወጣው ሰነድ ላይ ተመላክቷል።
ግዙፍና አዋጭ ሮኬቶችን የማምረቱን ስራ ትኩረት አደርግበታለሁ ያለችው ቤጂንግ፥ የማስወንጨፊያ ተሸከርካሪዎችም ዳግም ጥቅም ላይ በሚውሉ መሳሪያዎች እንዲሰሩ ለማድረግ አስባለች።
በሸንዙ 15 እና 16 ሳተላይቶች የሚገኙ የቻይና የህዋ ተመራማሪዎች በህዋ ላይ እየተንቀሳቀሱ ቅኝት ማድረግ እንደሚጀምሩ እና ተጨማሪ ተመራማሪዎች እና ሳተላይቶች ለማምጠቅ በትኩረት እንደምትሰራም ነው ቻይና በ2023 እቅዷ ያመላከተችው።