የቻይና ህዝብ ቁጥር ከ60 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀነሰ
የቻይና ህዝብ ለመጨረሻ ጊዜ ያሽቆለቆለው በፈረንጆቹ 1960 ሲሆን ይህም ሀገሪቱ ክፉኛ ረሀብ በገጠማት ጊዜ ነው
የህዝብ ቁጥር መቀነሱ ዓለም አቀፍ ምጣኔ-ሀብታዊ አንድምታ ይኖረዋል ተብሏል
የቻይና ህዝብ በስድስት አስርት ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀንሷል። በሀገሪቱ የስነ-ህዝብ ቀውስ ላይ የመጨረሻው የማስጠንቀቂያ ደወልም ነው ተብሏል።
በፈረንጆቹ 2022 የቻይና ህዝብ ቁጥር ባለፈው ዓመት ከነበረበት በ850 ሽህ በመቀነስ ወደ አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ዝቅ ማለቱን የመንግስት መረጃ ያሳያል።
ይህም ከ1960ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ የሊቀ-መንበር ማኦ ዜዶንግ አስከፊ ፖሊሲዎች ለረሀብ እና ሞት ምክንያት ሆነውበታል ከተባለው ጊዜ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ማሽቆልቆሉን ያሳያል።
ቻይና በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ በህዝብ ብዛት የነበራትን ቦታ በህንድ እንደምትነጠቅ ይጠበቃል። ይህ ለውጥ የሀገር ውስጥ እድገት እያደናቀፈ ባለበት ወቅት ዓለም አቀፍ ምጣኔ-ሀብታዊ አንድምታ ይኖረዋል ሲል ዘ ቴሌግራፍ ዘግቧል።
ቤጂንግ ባለፈው ዓመት የሀገሪቱ አጠቃላይ ምርት በሦስት በመቶ ማደጉን አስታውቃለች። ይህም ከመንግስት የአምስት ነጥብ አምስት በመቶ እድገት ያነሰ ነው። ከፈረንጆቹ 1976 ጀምሮ የባህል አብዮት ካበቃበት ጊዜ ጀምሮ በጣም አዝጋሚውን የምጣኔ-ሀብት እድገትንም ይወክላል ተብሏል።
ለበርካታ አስርት ዓመታት የቻይና ምጣኔ-ሀብት በየዓመቱ በከፍተኛ ደረጃ ለማደጉ "እርካሽ የሰው ኃይል" ምስጋና ይቻረዋል።
ከዚህ ቀደም ፖሊሲ አውጪዎች የህዝቡ ቁጥር በፍጥነት እያደገ መምጣቱን በማሰብ የአንድ ልጅ ፖሊሲን ተግባራዊ አድርገዋል።
ቤጂንግ በፈረንጆቹ 2016 ጥንዶች እስከ ሦስት ልጆች እንዲወልዱ ፈቅዳለች።