በ2024 አዲስ ዓመት የመጀመሪያ ቀን በእያንዳንዱ ሰከንድ 4 ውልደትና 2 ሞት ይመዘገባል
ዛሬ በሚጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2023 ዓመት የዓለም ህዝብ ቁጥር በ75 ሚሊየን ማደጉ ተገለጸ።
የአሜሪካ የሕዝብ ቆጠራ ቢሮ ባወጣው መረጃ የዓለም ህዝብ ቁጥር ባለፈው ዓመት በ75 ሚሊየን አድጓል ያለ ሲሆን፤ በአዲሱ አመት ከ8 ቢሊዮን በላይ እንደሚሆን አስታውቋል።
ቢሮው በተጠናቀቀው 2023 ዓመት የዓለም ህዝብ እድገት 0.95 በመቶ እንደነበረም ነው ባወጣው መረጃ ያስታወቀው።
በነገው እለት በሚጀምረው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት 2024 የመጀመሪያ ቀን ላይም የዓለም ህዝብ ቁጥር 8 ቢሊየን 19 ሚሊየን 876 ሺህ 189 እንደሚሆን ገልጿል።
በ2024 አዲስ ዓመት የመጀመሪያ ቀን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየእያንዳንዱ ሰከንድ 4 አዳዲስ ውልደቶች እና 2 ሞት ይጠበቃል ነው የተባለው።
የአሜሪካ የሕዝብ ቆጠራ ቢሮ አያይዞም በተጠናቀቀው 2023 የአሜሪካ የህዝብ ቁጥር በ0.53 መጨመሩን አስታውቋል።
በዚህም በ2023 የአሜሪካ ህዝብ ቁጥር በ1 ነጥብ 7 ሚሊየን አድገት አሳይቷል ያለው ቢሮው፤ በ2024 አዲስ ዓመት የመጀመሪያ ቀንም የአሜሪካ የህዝብ ቁጥር 335.8 ሚሊየን እንደሚሆን አመላክቷል።
ባለፉት አስር ዓመታት የአሜሪካ የህዝብ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እንደቀነሰ ነው የቢሮው መረጃ የሚያመለክተው።
በ2024 መጀመሪያ ላይ በአሜሪካ በየእያንዳንዱ ሰከንድ አንድ ልጅ እንደሚወለድ እና በ9.5 ሰክንድ ውስጥ እንደ ሰው እንደሚሞት የአሜሪካ የሕዝብ ቆጠራ ቢሮ መረጃ ያመለክታል።
ነገር ግን በስደተኞች ምክንያት የአሜሪካ ህዝብ ቁጥር ከመቀነስ እንደሚድንም ተገልጿል።
በአለምአቀፍ ፍልሰት መጠን መሰረት በየ28.3 ሰከንድ አንድ ሰው ወደ አሜሪካ ህዝብ ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል።