ቻይና ጦርነት ቢከሰት በሚል የመጠባበቂያ ነዳጅ እና ምግብ እያከማቸች ነው ተብሏል
ቻይና ኢኮኖሚዋን ለጦርነት እያዘጋጀች እንደሆነ ተገለጸ።
ታይዋን የቻይና አንድ አካል ነች የሚል ጽኑ አቋም ያላት ቻይና ከዚህ በተቃራኒ አመለካከት ካላቸው ምዕራባዊያን ሀገራት ጋር መካረር ውስጥ ገብታለች።
አሜሪካ ታይዋን ሉዓላዊ ሀገር ናት ብላ እውቅና ባትሰጥም የቻይና አንድ አካል ናት ብላ ግን እንደማታምን ተገልጿል።
ሁለቱ የዓለማችን ልዕለ ሀያል ሀገር አሜሪካ እና ቻይና በታይዋን ጉዳት ወደ ጦርነት እንዳያመሩ ተሰግቷል።
ሉዓላዊነቴን ለማስከበር ማንኛውንም እርምጃ እወስዳለሁ የምትለው ቻይና በታይዋን ጉዳይ ወደ ጦርነት ልትገባ እንደምትችልም ተገልጿል።
ቻይና በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በታይዋን አቅራቢያ ተደጋጋሚ የጦር ልምምድ በማድረግ ላይ ትገኛለች።
የቤጂንግን ድርጊት ተከትሎም አሜሪካ ለታይዋን ወታደራዊ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ ተጨማሪ ወታደሮቿን ወደ እስያ በማሰማራት ላይ ናት።
ይህን ተከትሎም በታይዋን ጉዳይ ወደ ጦርነት ልገባ እችላለሁ የምትለው ቻይና ቅድመ ዝግጅት እያደረገች መሆኗን አስታውቃለች።
ቻይና ወደ ጦርነት ብትገባ እና ከንግድ መነጠል ቢያጋጥም በሚል አማራጭ የመገበያያ መንገዶችን እየሞከረች እንደሆነ ተገልጿል
እንደ ኢኮኖሚስት ዘገባ ከሆነ ቻይና ወደ ጦርነት እገባለሁ በሚል ለዓመታት ሊያገለግል ይችላል በሚል የነዳጅ፣ ስንዴ እና ሌሎች ምግብ ነክ ምርቶችን እያከማቸች ነው ተብሏል።
በተለይም ስንዴ፣ በቆሎ፣ ሩዝ፣ አኩሪአተር እና ሌሎች የግብርና ምርቶችን በብዛት ወደ ሀገሯ እያስገባች እንደሆነ ተገልጿል።
ቻይና አሁን ላይ ለ18 ወራት የሚበቃ ስንዴ ከዝናለች የተባለ ሲሆን በጦርነቱ ምክንያት የንግድ ማዕቀብ ቢጣል ይህን መቋቋም የሚያስችል አዲስ የግብይት ስርዓት እየዘረጋች ነውም ተብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም በምዕራባዊያን የንግድ አማራጮች ላይ የመሰረቱ የቻይና የንግድ ተቋማት ከዚህ ጥገኝነት ለመላቀቅ ቀስ በቀስ ለመውጣት እየጣሩ እንደሆነም ተገልጿል።
እነዚህ የንግድ ተቋማት የመጠባበቂያ ገንዘብ ክምችታቸውን ከዶላር እና ዩሮ ይልቅ ወደ ወርቅ በመቀየር ላይ ናቸውም ተብሏል።
ይሁንና ቻይና በይፋ በታይዋን ጉዳይ ወደ ጦርነት ለመግባት ዝግጅት እያደረገች ነው መባሏን እስካሁን በይፋ ያለችው ነገር የለም።