ፖለቲካ
ቻይና በሰብዓዊ መብት ስም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚደረጉ ጥረቶችን ተቸች
ምክትል ጠ/ሚ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከቻይና ምክር ቤት አባልና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ጋር በስልክ ተወያይተዋል
በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት አቋሟ ጸንታ እንደምትቀጥልም አስታውቃለች
ቻይና በሰብዓዊ መብት ስም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚደረገውን ጥረት ተቸች።
ቻይና በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት
አቋሟ ጸንታ እንደምትቀጥልም አስታውቃለች።
ምክትል ጠ/ሚ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከቻይና መንግስት አማካሪ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ጋር በስልክ ተወያይተዋል።
በውይይቱ መንግስት በትግራይ ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም፣ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት እና ህዝባዊ ውይይቶችን ለማመቻቸት እንዲሁም አርሶደአሮችን ለመደገፍ የተቻለውን ሁሉ እያደረገ መሆኑን የገለጹት አቶ ደመቀ ተፈጽመዋል የተባሉ ጥፋቶችን ለማጣራትና ጥፋተኞችን ተጠያቂ ለማድረግ ሰብዓዊ ድጋፎችን ለማድረግ ጭምር እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
ሆኖም የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ስጋት ለመመለስ በሚያስችሉ በእነዚህ ሁሉ ጥረቶች መካከል የውሸት ዘመቻዎች አሁንም ሊቆሙ አለመቻላቸውን ነው አቶ ደመቀ የገለጹት።
የቻይና ህዝብና መንግስት ይህን የኢትዮጵያን ጥረት እንደሚረዱ ያላቸውን ሙሉ እምነትም ገልጸዋል።
በትግራይ የመልሶ ግንባታ ጥረቶች መንግስትን ያወደሱት ዋንግ ዪ በበኩላቸው
በሰብዓዊ መብት ስም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚደረገውን ጥረት ተችተዋል።
ሃገራቸው በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት አቋሟ ጸንታ እንደምትቀጥልም ነው የተናገሩት።
የግድቡን የሶስትዮሽ የድርድር እና አፍሪካ ህብረት መር መፍትሔዎችን በተመለከተው ንግግራቸውም ዋንግ ዪ ሃገራቸው የጋራ መፍትሔዎችን ለመፈለግ የሚደረጉ ጥረቶችን እንደምትደግፍ ተናግረዋል።
እንደጋራ ወዳጅ ሃገር ቻይና በሱዳን ድንበር ጉዳይ ለሰላማዊ መፍትሔዎች ግፊት እንደምታደርግም አስታውቀዋል።
የስልክ ውይይቱ ስለመጪው ሃገር አቀፍ ምርጫ በመነጋገር መጠናቀቁንም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ አመልክቷል።