ዛሬ 80ኛ አመቱን ያከበረው አዲስ ዘመን ጋዜጣ በመጀመሪያ እትሙ ምን አስነብቦ ነበር?
አዲስ ዘመን ጋዜጣ ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው ግንቦት 30 ቀን 1933ዓ.ም ነበር
አዲስ ዘመን ጋዜጣ በመጀመሪያ እትሙ የፊት ገጽ ይዞ የወጣው የድል ዜና ምን ነበር?
በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ስር ከሚታተሙት ዕለታዊ ጋዜጦች መካከል አንዱ የሆነው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዛሬ 80 ዓመት ሞልቶታል፡፡ጋዜጣው ሕትመት የጀመረው የወቅቱ ንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ በስደት ከቆዩባት እንግሊዝ ሀገር ከተመለሱ ከአንድ ወር በኋላ ግንቦት 30 ቀን 1933 ዓ.ም ነው፡፡
ንጉሰ ነገስቱ በድል አድራጊነት መንፈስ ከስደት የተመለሱት ኢትዮጵያን ለ5 አመታት በወረራ ይዞ የነበረው ጣሊያን ተሸንፎ ከሀገር መውጣቱን ተከትሎ ነበር፡፡
አዲስ ዘመን ጋዜጣ በመጀመሪያው ዕትሙ አንድ ትልቅ ፎቶ ይዞ ወጥቶ ነበር፡፡ ይህ ፎቶ ንጉሱ በአውቶሞቢል በክብር ወደ አዲስ አበባ ሲገቡ ያሳያል፡፡ ከዚህ ባለፈም የጋዜጣው የመጀመሪያው ዕትም የዜና ርዕሱ “የአዲስ ዘመን ጋዜጣ መጀመር” ይላል፡፡ “ይህ አዲስ ዘመን ተብሎ የተሰየመው ጋዜጣ ከዛሬ ጀምሮ ወደፊት ለመላው ኢትዮጵያውያን የረዳትነቱን ስራ ይሰራ ዘንድ ተመሰረተ“ የሚለው ደግሞ የጋዜጣው የመጀመሪያ ዜናው መሪ አንቀጽ ነው፡፡
ጋዜጣው “አዲስ ዘመን” የሚለውን ስያሜ ያገኘው ንጉሰ ነገሥቱ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም አዲስ አበባ ሲገቡ ከተናገሩት ንግግር ጋር የተያያዘ እንደሆነ የጋዜጣው የመጀመሪያ ዕትም ያሳያል፡፡
ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ከስደት ከቆዩበት እንግሊዝ ተመልሰው አዲስ አበባ ሲገቡ ባደረጉት ንግግር “ከማናቸውም አስቀድሞ ለሁላችሁም ልነግራችሁና ልትረዱት የምፈልገው ይህ ቀን ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ የአዲስ ዘመን መክፈቻ መሆኑን ነው፡፡ በዚህም በአዲስ ዘመን ሁላችን መፈፀም ያለብን አዲስ ስራ ይጀመራል“ ብለው ስለነበር ጋዜጣውም “አዲስ ዘመን“ ተብሎ እንደተሰየመ ይነገራል፡፡
የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የመጀመሪያው ዕትም የጋዜጣውን አጀማመር የሚገልጽ ነው፡፡ “ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ለኢትዮጵያ አዲስ በሆነው ዘመን ለአገርና ለሕዝብ ጥቅም የሚያስፈልገውን ስራ ሁሉ እያመለከተ፤ይልቁንም ሕዝብ ለአገሩ፣ ለመሪውና ለንጉሰ ነገሥቱና ለንጉሰ ነገሥቱም መንግሥት ማድረግ የሚገባውን እየገለፀ የበጎን ስራ መንገድ የሚመራ እንዲሆን ይህ ጋዜጣ በግርማዊ ንጉሰ ነገሥት ተመሰረተ“ የሚለው ግንቦት 30 ቀን 1933 ዓ.ም የአዲስ ዘመን ጋዜጣ አጀማመር ከሚለው ርዕስ ስር የሚገኝ አንቀጽ ነው፡፡
በዚሁ ዕለት ዕትምም “ስራውም በሦስት ቃሎች ይጠቀለላል፡፡ እውነት፣ ረዳትነትና አገልግሎት፡፡ እውነት ስንል በዚህ ጋዜጣ የሚነገረው ነገር ሁሉ መሰረቱ በፍጹም እውነትን እየተከተለ ለአንድ ጥቅም ብቻ ያልሆነና ለመላው ጥቅም የሚሰራ እንዲሆን ነው”ይላል፡፡
ጋዜጣው በዚሁ እትሙ “ራሳቸውን መስዋዕት አድርገው የራሳቸውን ጥቅም ሁሉ አስወግደው ለሕዝባቸውና ለአገራቸው“ ለደከሙት “ለተወደዱ ንጉሰ ነገሥታችንና ላቆሙት መንግሥት የሚያገለግል እንዲሆን ነው“ መመስረቱንም ይገልጿል፡፡
ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ፤ ሚያዝያ 27 ቀን አዲስ አበባ ገብተው ለሕዝባቸው ሲናገሩ “ከማናቸውም አስቀድሞ ለሁላችሁም ልነግራችሁና ልትረዱት የምፈልገው ይህ ቀን ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ የአዲስ ዘመን መክፈቻ መሆኑን ነው፡፡ በዚህም በአዲስ ዘመን ሁላችን መፈፀም ያለብን አዲስ ስራ ይጀመራል“ ብለው ነበር፡፡
አዲስ ዘመን ጋዜጣ፤ ከ1933 ዓ.ም ጀምሮ፣ ለ80 ዓመታት ያህል ሕትመቱ ሳይቋረጥ፣ እስከዛሬ ድረስ በአማርኛ ቋንቋ እየታተመ ለአንባቢያን በመድረስ ላይ ነው፡፡ በንጉሠ ነገስቱ ዘመን፤ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በቀን 10 ሺ ይታተም እንደነበር ታሪክ ያስረዳል፡፡ ጋዜጠው 60ኛ አመቱን ባከበረበት 1993 ዓ.ም ዕለታዊ ሕትመቱ 40ሺ ነበር።
ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ የይዘትና የቅርጽ ለውጥ አድርጓል፡፡ ጋዜጣው በቀን 10 ሺ ኮፒ እንደሚያትም ተገልጿል፡፡ ጋዜጣው በኢትዮጵያ 10 ብር ይሸጣል፡፡
የአዲስ ዘመን ጋዜጣ፤ ሕትመት የጀመረበት 80ኛ ዓመት ዛሬ በአዲስ አበባ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡በዝግጅቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ታዋቂ ግለሰቦችና ምሁራን ተገኝተዋል፡፡