በኮሮና ቫይረስ ከፍተኛው ሞት በተከሰተበት በትናንትናው እለት የ108 ሰዎች ህይወት አለፈ
ኮሮና ቫይረስ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ትልቁ ሞት የተከሰተው በትናንትናው እለት ነው፡፡ ትናንት የሞቱትን 108 ሰዎች ጨምሮ የሟቾቹ ቁጥር በቻይና 1,017 ደርሷል፡፡
በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ በቻይና 42,708 ሲደርስ ከቻይና ውጭ 390 ደርሷል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ሪፖርት በቻይና ከትናንት በስቲያ ከነበረው 3,062 ከነበረው 20 በመቶ ቀንሶ ትናንት 2,478 መሆኑ አንድ ተስፋ ሰጪ ዜና ሆኗል፡፡
እስካሁን በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር በ2003 እዚያው ቻይና ተከስቶ ከነበረው ሳርስ የተሰኘ ቫይረስ በከፍተኛ ቁጥር በልጧል፡፡ ሳርስ በወቅቱ 774 ሰዎችን እንደገደለ ነው ሪፖርት የተደረገው፡፡
የቻይና መንግስት ለበሽታው ተገቢውን ምላሽ አልሰጡም ያላቸውን ባለስልጣናት ከኃላፊነት እያነሳ ነው፡፡ ቫይረሱ የተከሰተበት የሁቤይ ግዛት ጤና ኮሚሽን ኃላፊ እና በኮሚሽኑ የኮሚዩኒስት ፓርቲ ጸኃፊ ከኃላፊነታቸው ከተነሱት መካከል ናቸው፡፡
ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ በቤጂንግ ሆስፒታል ጉብኝት እያደረጉ
የዓለም ጤና ድርጅት ኤክስፐርቶችን ያካተተ አጥኚ ቡድን ወደ ቻይና ልኳል፡፡ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሀኖም እንዳሉት፣ ቡድኑ በቅርቡ ወደ ቻይና ለሚላከው ዓለማቀፍ የጤና ቡድን ጥርጊያ መንገድ የሚያዘጋጅ ነው፡፡
ከቻይና ውጭ ባሉ ሀገራትም የተጠቂዎች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ ነው፡፡ የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ አንድ ተጨማሪ ሰው በኮሮና ቫይረስ መያዙን አረጋግጣለች፡፡ ይሄም በሀገሪቱ የተጠቂዎችን ቁጥር 8 አድርሶታል፡፡ አንድ የ73 ዓመት ቻይናዊ አዛውንት ደግሞ በሀገሪቱ ከቫይረሱ ማገገማቸው ተጠቁሟል፡፡
ቬትናምም አንድ የ3 ወር ህጻንን ጨምሮ 2 ተጨማሪ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸን አስታውቃለች፡፡ አጠቃላይ ተጠቂዎችም በሀገሪቱ 15 ደርሰዋል፡፡
ዩናይትድ ኪንግደምም ትናንት 4 ተጠቂዎችን አግኝቻለሁ ያለች ሲሆን የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር በሀገሪቱ ወደ 8 ከፍ ብሏል፡፡
የቫይረሱ ተጠቂዎች ከተገኙበት ወዲህ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ጃፓን አካባቢ 3,700 ሰዎችን ጭኖ በመጓዝ ላይ እንዳለ እንዳይንቀሳቀስ የታገደው ዳያመንድ ፕሪንሰስ ከሩይዝ መርከብ ትናንት 65 ተጠቂዎች ተገኝተውበታል፡፡ እስካሁን በመርከቡ ውስጥ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር 135 ደርሷል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ዋና ዋና ምልክቶች ከፍተኛ የሙቀት ስሜት እና የአየር እጥረት ወይም የመተንፈስ ችግር ናቸው፡፡ ቫይረሱ ካለበት ሰው ጋር የቅርብ ግንኙነት አለማድረግ፣ እጅን ቶሎ ቶሎ ባሳሙና መታጠብ፣ ባልታጠበ እጅ ዐይን፣ አፍንጫና አፍን አለመነካካት፣ ተጠቂዎች ባሉበት አካባቢ ለምሳሌ በሆስፒታል ውስጥ ጭምብል የሚያደርጉ ሰዎች ጭምብሉን በአግባቡ መጠቀም፤ ማለትም ጭምብሉን ሲያወልቁ በተነካካ እጃቸው በተለይ ፊታቸው አካባቢ የሚገኙ የሰውነት ክፍላቸውን አለመነካካት ቫይረሱን ለመከላከል ይረዳሉ የተለያዩ የዜና ምንጮች እንደዘገቡት፡፡