የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመግታት 675 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተባለ፡፡
ከኮሮና ቫይረስ ሟቾች መካከል 564ቱ ቻይናውያን ሲሆኑ አንዱ ፊሊፒናዊ ነው፡፡ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥርም በቻይና ከ28 ሺ በላይ በሌሎች ቫይረሱ የተዳረሰባቸው 25 ሀገራት ደግሞ ከ260 በላይ ሆኗል፡፡
ከ1,100 በላይ ሰዎች ከበሽታው ማገገማቸውም ተገልጿል፡፡
ኮሮና ቫይረስ ያለባት ቻይናዊት እናት የወለደችው የ30 ሰዓታት እድሜ ያለው ህጻን ቫይረሱ እንደተገኘበት መረጋገጡ የቫይረሱ መተላለፊያ መንገዶች ሰፊ መሆናቸውን ማሳያ ሊሆን ይችላል እየተባለ ነው፡፡
ህጻኑ እስካሁን በእድሜ ትንሹ የቫይረሱ ተጠቂ ነው፡፡ አብዛኛው ተጠቂዎች በሚገኙበትና የኮሮና ቫይረስ መነሻ በሆነችው ዉሀን ከተማ በሚገኝ ሆስፒታል ነው ህጻኑ የተወለደው፡፡ ይሁንና ህጻኑ በማህጸን ውስጥ አሊያም ከተወለደ በኋላ በቫይረሱ ስለመያዙ የታወቀ ነገር የለም፡፡
አሁን ላይ በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛል የተባለው ይህ ህጻን የህክምና ክትትል እየተደረገለት ነው ሲሲቲቪ እንደዘገበው፡፡
የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር እና ደካማ የጤና ስርዓት ያላቸውን ሀገራት ለመደገፍ 675 ሚሊዮን የኣሜሪካ ዶላር እንደሚያስፈልግ የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሀኖም እንዳሉት ከተባለው ገንዘብ 61.5 ሚሊዮን ዶላር ድርጅቱ ቫይረሱን ለመቆጣጠር ለሚያከናውነው ስራ የተቀረው አብዛኛው ገንዘብ ደግሞ የቫይረሱ ከፍተኛ ተጠቂ ለሆኑ ሀገራት የሚሰጥ ነው፡፡
እስካሁን ቫይረሱን ለመከላከል በሚል በትንሹ 25 አየር መንገዶች ወደ ቻይና እና ከቻይና ውጭ የሚያደርጉትን በረራ አቁመዋል አሊያም ቀንሰዋል፡፡
ወደ ቻይና ከሚደረግ በረራ ጋር በተያያዘ ትናንት ጥር 27 ቀን 2012 ዓ.ም ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገ/ማሪያም በረራ ማቆም መፍትሄ እንደማይሆን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም አየር መንገዱ የዓለም ጤና ድርጅት ያስቀመጠውን መርህ በመከተል አስፈላጊዉን ጥንቃቄ በማድረግ በረራውን እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተጠረጠሩ 4 ሰዎች በደቡብ አፍሪካ በተደረገላቸው ምርመራ ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው ትናንት መረጋገጡም ይታወሳል፡፡
ለዘገባው የተለያዩ የዜና ምንጮችን ተጠቅመናል፡፡