ከቻይና ውጭ በኮሮና ቫይረስ የመጀመሪያው ሞት በፊሊፒንስ ተከሰተ፡፡
በፊሊፒንስ በኮሮና ቫይረስ የሞተው የ44 ዓመት ቻይናዊ ጎልማሳ የመጀመሪያው ከቻይና ውጭ በቫይረሱ የሞተ ግለሰብ ሆኗል፡፡ ግለሰቡ ከቻይና የቫይረሱ መነሻ ሁቤይ ግዛት ወደ ፊሊፒንስ ያቀና ነው፡፡
በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሰጠው የዓለም ጤና ድርጅት ሟቹ ፊሊፒንስ ከመግባቱ በፊት በቫይረሱ የተጠቃ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ከሟቹ ጋራ ወደ ሀገሪቱ የተጓዘችው ሌላ የ38 ዓመት ቻይናዊትም ቫይረሱ ተገኝቶባታል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በርካታ ፊሊፒናውያን ስጋት አድሮባቸው፣ የአፍና አፍንጫ ጭምብሎችን ተሻምተው በመግዛት ላይ ናቸው፡፡
ይሁን እንጂ በፊሊፒንስ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ራቢንድራ አቤያሲንጌ ህብረተሰቡ እንዲረጋጋ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ “ምንም እንኳን በሀገሪቱ የተከሰተው ሞት ከቻይና ውጭ የመጀመሪያው ቢሆንም ሟቹ ከቻይና የመጣ እንጂ ቫይረሱ እዚሁ ተከስቶ አይደለም ህይወቱ ያለፈው” ብለዋል ተወካዩ፡፡
በአጠቃላይ የኮሮና ቫይረስ ሟቾች ቁጥር እስካሁን 305 ሲደርስ በቫይረሱ የተያዙት ደግሞ ከ 14,400 በላይ ሆነዋል፡፡
የቫይረሱ ስርጭት ከ25 ሀገራት በላይ እንደደረሰም ዘገባዎች ያሳያሉ፡፡ ከነዚህም አሜሪካና አውስትራሊያን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ከቻይና የሚመጡ የውጭ ሀገራት ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዳይገቡ ሲያግዱ የራሳቸው ዜጎች ደግሞ በተለየ ማዕከል ውስጥ እንዲቆዩ እያደረጉ ነው፡፡
ኒው ዝላንድ፣ ጃፓን፣ ሩሲያ፣ ፓኪስታን፣ ጣሊያን እና ሲንጋፖርም ተመሳሳይ እገዳ የጣሉ ሀገራት ናቸው፡፡ ደቡብ ኮሪያ ደግሞ ቫይረሱ መከሰቱ ከተረጋገጠበት ጊዜ ጀምሮ በቻይና የቫይረሱን መነሻ ዉሀን ከተማን የጎበኘ ማንኛውም የውጭ ሀገር ዜጋ ሀገሯ እንዳይገባ ከልክላለች፡፡
የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ አምስተኛ የቫይረሱ ተጠቂ የተገኘባት ሀገር ስትሆን፣ ዜጎቿ ስጋት እንዳይገባቸው አሳስባለች፡፡ ከዉሀን የመጣውን አምስተኛውን ተጠቂ ጨምሮ ከዚህ ቀደም ምልክቱ የታየባቸው 4 ቻይናውያን የአንድ ቤተሰብ አባላትም በተለየ ስፍራ ህክምና በመከታተል ላይ መሆናቸውን የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል፡፡
ጭምብል ያደረጉ ቱሪስቶች በዱባይ
አሁን ላይ ከቫይረሱ ስጋት ጋር በተያያዘ ወደ ቻይና በረራ ማድረግ ያቆሙ አየር መንገዶች ከ 10 በላይ ደርሰዋል፡፡
የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት በቻይና ዉሀንን ጨምሮ በሁቤይ ግዛት እና አካባቢው የሚገኙ ከተሞች ዛሬም ድረስ እንደተዘጉ ናቸው፡፡
በዉሀን ሲገነባ የነበረው ባለ 1,000 አልጋ የኮሮና ቫይረስ ሆስፒታል ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን የሀገሪቱ ቴሌቪዥን ሲሲቲቪ ዘግቧል፡፡ ከነገ ጥር 25 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ 1,400 የህክምና ባለሙያዎች በሆስፒታሉ አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉም ተብሏል፡፡
በዉሀን ምንም አይነት አንገብጋቢ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎች እንዳይደረጉ ተከልክለዋል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ግን የእንቅስቃሴ እገዳ ከተጣለባቸው ከተሞች፣ ሰዎች በህገወጥ መንገድ እየተዘዋወሩ በሽታው ሊስፋፋ ስለምችል ከሙሉ እገዳ ይልቅ ምርመራ እየተደረገላቸው እንዲንቀሳቀሱ መደረግ አለበት ብሏል፡፡
ቫይረሱ ያልጠበቀችው ፈተና ውስጥ የከተታት ቻይና አለማቀፉ ማህበረሰብ የህክምና ቁሳቁስ እና መሰል ድጋፍ እንዲያደርግላት በመጠየቅ ላይ ናት፡፡
በርካታ ተመራማሪዎች ለቫይረሱ መድሀኒት ለማግኘት ሰፊ ምርምር በማድረግ ላይ ቢሆኑም እስካሁን ክትባትም ይሁን ምንም አይነት መድሀኒት አልተገኘለትም የተለያዩ የዜና አውታሮች እንደዘገቡት፡፡