የኮሮና ቫይረስ ሟቾች ቁጥር በአንድ ቀን ልዩነት በ65 ጨምሮ 427 ደረሰ፡፡
በቫይረሱ ከሞቱት 425ቱ ቻይናውያን ናቸው፡፡ አንዱ የቻይና ራስ ገዝ አስተዳደር የሆንግኮንግ ነዋሪ ሲሆን ሌላኛው አንድ ሟች ደግሞ ፊሊፒናዊ ነው፡፡
በትናንትናው እለት ብቻ 65 ሰዎች የሞቱ ሲሆን ይሄም እስካሁን በቫይረሱ በአንድ ቀን የተከሰተ ከፍተኛው የሞት ቁጥር ነው፡፡
የተጠቂዎች ቁጥር በቻይና 20,471 ሲደርስ በሌሎች ሀገራት ደግሞ 159 ደርሷል፡፡ በአንድ ቀን ልዩነት በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ከ3,200 በላይ (18%) ጨምሯል፡፡ ይሄም ቫይረሱ ምንም የመቀነስ አዝማሚያ እንደማያሳይ የሚያመላክት ነው፡፡
80 በመቶ የቫይረሱ ተጠቂዎች እድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ ነው፡፡ ሌላ በሽታ ያለባቸው ግለሰቦች ደግሞ ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው፡፡ ከተጠቂዎች መካከል 75 በመቶው ሌላ ተጨማሪ ህመም የነበረባቸው መሆኑ ለዚህ ሁነኛ ማሳያ ነው፡፡
እስካሁን ከሞቱት መካከል 97 በመቶው ቫይረሱ የተከሰተበት የሁቤይ ግዛት ነዋሪዎች ናቸው፡፡
በተለያዩ 25 ሀገራት 159 የቫይረሱ ተጠቂዎች መገኘታቸው የቫይረሱን ስርጭት አሳሳቢ ያደረገው ሲሆን ከዚህ ጋር ተያይዞ በርካታ ሀገራት ወደ ቻይናና ከቻይና ውጭ በተለያየ መጠን የጉዞ እገዳ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
ከእስካሁን የጉዞ እገዳ እርምጃዎች ጠንከር ያለው ደግሞ የዩኤስ አሜሪካ ነው፡፡ ሀገሪቱ ባለፉት 2 ሳምንታት ቻይናን የጎበኘ ማንኛውም የውጭ ሀገር ዜጋ ምድሯን እንዳይረግጥ ከልክላለች፡፡ ይህ እርምጃዋ አሜሪካን በውስጥም በውጭም ለተቃውሞና ትችት ዳርጓታል፡፡
ቻይና የአሜሪካን ውሳኔ ስጋትን ለማባባስ የተወሰደ የተጋነነ እርምጃ ስትል አጣጥላዋለች፡፡ አሜሪካ ቫይረሱን ለመከላከል ምንም ድጋፍ ሳታደርግ ስጋት ለመፍጠር ብቻ በመትጋት ላይ እንደምትገኝም ነው ቻይና የገለጸችው፡፡
የዓለም ጤና ድርጅትም የአሜሪካን መሰል እርምጃዎች የቫይረሱን ስርጭት ከመግታት ይልቅ የማባባስ እድላቸው ሰፊ እንደሚሆን በመግለጽ ሀገራት የሚጥሉትን የጉዞ እገዳ ማቆም እንዳለባቸው አሳስቧል፡፡
ቫይረሱ እየተሰራጨ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ በአንዳንድ ሀገራት ቻይናውያንን መፍራትና ማግለል እየተስተዋለ ነው፡፡
በቬትናም ቻይናውያንን አናስተናግድም የሚል ማስታወቂያ በሬስቶራንቶች
ስለ ዉሀን ኮሮና ቫይረስ እስካሁን ሳይንቲስቶች የማያውቋቸው በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ ይሄም በመላው ዓለም ለቫይረሱ ክትባትና መድሀኒት ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት ከባድ አድርጎታል ነው የተባለው፡፡
በጣሊያን ለሙከራ የተዘጋጀ የኮሮና ቫይረስ ክትባት
ይሁንና የታይላንድ ባለስልጣናት በሰጡት መግለጫ የኤች.አይ.ቪ እና የወፍ ጉንፋን መድሀኒቶች ተቀላቅለው የተሰጣቸው ሁለተኛ የበሽታው ታማሚ ትናንት መዳናቸውን አስታውቀዋል፡፡ ቅይጥ መድሀኒቱን የወሰዱት የ71 ዓመቷ ቻይናዊት የቫይረሱ ተጠቂ አዛውንት ናቸው፡፡ መድሀኒቱ ፍቱን ስለመሆኑ ግን ከባለስልጣናቱ ተጨማሪ መረጃ እየተጠበቀ ነው፡፡
ምንጭ፡- ሲኤንኤን እና ሲጂቲኤን