የኮሮና ቫይረስ ሟቾች 362 የደረሱ ሲሆን የዉሀን የአስቸኳይ ጊዜ ሆስፒታል ዛሬ ስራ ጀምሯል፡፡
ቫይረሱ እስካሁን 362 ሰዎችን ሲገድል የተጠቂዎች ቁጥር ደግሞ በቻይና 17,238 በሌሎች 25 ሀገራት 148 ደርሷል፡፡
480 ሰዎች ከቫይረሱ አገግመዋል የተባለ ቢሆንም በድጋሚ የመጠቃታቸው አሊያም ቫይረሱ ሊያንሰራራ የሚችልበት እድል ከፍተኛ መሆኑን የጤና ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡
አሁን ኮሮና ቫይረስ በገዳይነቱ በቻይና ከሳርስ በልጧል፡፡ ሳርስ የተባለው ቫይረስ በ2003 በቻይና 349 ሰዎችን ለህልፈት መዳረጉ ይታወቃል፡፡
አገልግሎት አቅራቢ ግለሰብ በዉሀን
1,000 አልጋዎች ያሉት በዉሀን ከተማ የተገነባው የኮሮና ቫይረስ የአስቸኳይ ጊዜ ሆስፒታል ዛሬ ስራ ጀምሯል፡፡ ሆሼንሻን የሚል ስያሜ የተሰጠው ሆስፒታሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞች ሌት ተቀን ተረባርበው በ አንድ ሳምንት የገነቡት ነው፡፡
የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በሚል በቻይና ወደ 31 ግዛቶች የመጀመሪያ ደረጃ የአስቸኳይ ምላሽ ተግባር በማከናወን ላይ ነው፡፡
በተለይ በሁቤይ ግዛት እና አካባቢው የሚገኙ በርካታ ከተሞች የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሎባቸዋል፡፡ የቫይረሱ መነሻ የሆነችው ዉሀን ደግሞ ገደቡ ክፉኛ የጠነከረባት ከተማ ነች፡፡
የዉሀን ከተማ እንቅስቃሴ የተገደበ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ነዋሪዎቿ የእለትተለት አስፈላጊ ሸቀጦች እና ቁሳቁሶች በሀገሪቱ የጦር ሰራዊት አማካኝነት እየደረሳቸው ነው፡፡ አስፈላጊው የለትተለት የምግብ እና ሌሎች ቁሳቁሶች ለነዋሪዎቹ ያለማቋረጥ እንዲደርስ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡
11 የቫይረሱ ተጠቂዎች ያሉባት ዩኤስ አሜሪካ ስጋት ካየለባቸው የቻይና ግዛቶች ዜጎቿን ለማስወጣት ተከታታይ በረራዎች እንደምታደርግ የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ገልጸዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሜሪካ ቫይረሱን ከማጋነን ባለፈ ምንም ድጋፍ አላደረገችም ሲል ተችቷል፡፡ የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ሁአ ቹንዪንግ እንዳሉት ሀገራቸው ቫይረሱን ለመቆጣጠር በምታደርገው ጥረት የተለያዩ ሀገራት አድናቆትና ድጋፍ እየቸሩ በሚገኙበት በዚህ ወቅት አሜሪካ ስጋትን ከማባባስ ውጭ ምንም ድጋፍ አላደረገችም፡፡
በሌላ በኩል የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ለቻይና ያላትን ድጋፍ ለመግለጽ በዱባዩ የዓለማችን ትልቁ ህንጻ ቡርጅ ካሊፋ ላይ የቻይናን ሰንደቅ ዓላማ በብርሀን አሳይታለች፡፡ ሀገሪቱ ቻይና ቫይረሱን ለመቆጣጠር በምታደርገው ጥረት ድጋፍ እንደምታደርግም ነው ያሳወቀችው፡፡
የብሪታኒያው ግዙፍ የመድሀኒት አምራች ኩባኒያ ግላክሶ ስሚዝ ክላይን የኮሮና ቫይረስ ክትባት ለማዘጋለት ዘመናዊ ቴክኖሎጄ በመጠቀም ጥረት እያደረገ መሆኑን ይፋ አድርጓል፡፡
ምንጭ፡-ሲኤንኤን እና ሲጂቲኤን