በቻይና የመሬት መንቀጥቀጥ በ5 የሀይል ማመንጫ ግድቦች ላይጉዳት አደረሰ
በሬክተር ስኬል 6.8 የተመዘገበ ርዕደ መሬት ባስተናገደችው ቲቤት የሚገኙት ግድቦች አደጋ ሊፈጥር በሚችል ሁኔት ተጎድተዋል
የአካባቢው የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በግድቡ ግርጌ ስር የሚኖሩ ከ1500 በላይ ዜጎችን ወደ ሌሎች ስፍራዎች አዘዋውረዋል
በምዕራብ ቻይና ቲቤት ባለፈው ሳምንት በሬክተር ስኬል 6.8 የተመዘገበ ርዕደ መሬት መከሰቱን ተከትሎ በስፍራው የሚገኙ 5 የውሀ ሀይል ማመንጫ ግድቦች ላይ የመሰንጠቅ አደጋ መከሰቱ ተነግሯል፡፡
የአከባቢው የድንገተኛ አደጋ ምላሽ ባለስልጣን እንዳስታወቀው በስፍራው ከሚገኙ 14 የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ግድቦች መካከል በአምስቱ ላይ ችግሩ ተፈጥሯል፡፡
ይህን ተከትሎም በግድቦቹ ተፋሰስ እና አቅራቢያ የሚገኙ ከ1500 በላይ የ6 መንደር ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ተደርጓል፡፡
ከዚህ ባለፈም ጉዳት ካስተናገዱ ግድቦች መካከል ሶስቱ የያዙትን ውሀ ለማፋሰስ ጥረት እየተደረገ ሲሆን በቀሪዎቹ ግድቦች ላይ ደግም ክትትል እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡
የ126 ሰዎችን የቀጠፈው ርዕደ መሬት በህንድ እና ቻይና አካባቢ የሚገኙ የሀይል ማመንጫ ግድቦች ከፍተኛ ስጋት እንደተደቀነባቸው አመላካች ነው ሲል ሬውተርስ ዘግቧል፡፡
በነዚህ አካባቢዎች ከዚህ ቀደም የተከሰቱ የርዕደ መሬት አደጋዎች፣ የመሬት መንሸራተት እና የድንጋይ ናዳ በግድቦች ላይ ጉዳት አድርሰዋል።
እ.ኤ.አ. በ 2015 በኔፓል የተከሰተው ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ በግድብ ላይ ያደረሰው ጉዳት ከአንድ አመት ለሚበልጥ ጊዜ ሀገሪቱ ከውሀ የምታገኘው አንድ አምስተኛ ሀይል እንዲቋረጥ ማድረጉ የሚታወስ ነው።
በ2008 በቻይና ከተከሰተው ርዕደ መሬት ቀጥሎ በአደገኛነቱ በአምስተኛ ደረጃ የተቀመጠው የባለፈው ሳምንት የመሬት መንቀጥቀጥ 3600 ቤቶችን እና ሀይማኖታዊ ተቋማትን ያፈረሰ ሲሆን ፤ በአካባቢው በሬክተር ስኬል እስከ 5.0 የሚደርስ ርዕደ መሬት መቀጠሉ ተሰምቷል፡፡
የደቡባዊ ቻይና ፣ ኔፓል እና ሰሜናዊ ህንድ አካባቢ በሚፈጠር የመሬት ውስጥ እንቅስቃሴ እና የቅልጥ አለት ፍጭት ምክንያት ተደጋጋሚ መሰል አደጋዎችን ያስተናግዳሉ፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ በርካታ የመሬት መንቀጥቀጦችን ከሚያስተናግዱ ሀገራት መካከል ቻይና ቀዳሚዋ እንደሆነች መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡