በቻይና ቲቤት ግዛት ውስጥ በደረሰው የርዕደ መሬት አደጋ የሟቾች ቁጥር ከ120 አለፈ
ከ1800 በላይ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች እና 1600 ወታደሮች አደጋው ወደተከሰተበት ግዛት ተሰማርተዋል
ርዕደ መሬቱ ከተከሰተ ከ 24 ሰአታት በኋላ በፍርስራሽ ውስጥ የነበሩትን ለማውጣት በቦታው የነበረው ከባድ ቅዝቃዜ የነፍስ አድን ስራ ለመስራት ከባድ ሆኗል
በቻይና ቲቤት ግዛት ውስጥ በደረሰው የርዕደ መሬት አደጋ የሟቾች ቁጥር ከ120 አለፈ።
በቻይናዋ በሂማላያ ተራሮች ስር በምትገኘው ቲቤት ግዛት ውስጥ በተከሰተው ከባድ የርዕደ መሬት አደጋ ምክንያት መውጫ አጥተው የነበሩት ከ 400 በላይ ሰዎች መውጣታቸውን የቻይና ባለስልጣናት በዛሬው እለት አስታውቋል። ነገርግን ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም ተብሏል።
በትናንትናው እለት የተከሰተው መጠኑ በሬክተር 6.8 የተለካው የርዕደ መሬት አደጋ በግዛቷ በቅርብ አመታት ውስጥ ከተከሰቱት ውስጥ እጅግ ኃይለኛ የሚባል ሲሆን በአለም ትልቅ ከሆነው የኢቨረስት ተራራ 80 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ቲቤት ውስጥ ትንግሪ በተባለች ቦታ ነው የተነሳው።
አደጋው በጎረቤት ቡትሀን፣ ህንድ እና ናፓል ህንጻዎችን አንቀጥቅጧል።
ርዕደ መሬቱ ከተከሰተ ከ 24 ሰአታት በኋላ በፍርስራሽ ውስጥ የነበሩትን ለማውጣት በቦታው የነበረው ከባድ ቅዝቃዜ ካምቦዲያን በምታክለው ቦታ የነፍስ አድን ስራ ለመስራት ከባድ ሆኖ ነበር።
ከፍታ ባላቸው ቦታዎች የሙቀት መጠኑ እስከ ኔጋቲቪ 18 ዲግሪ ሴልሺየስ ድረስ ወርዶ ነበር። ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ መውጫ ያጡ ወይም መጠለያ የሌላቸው ሰዎች ለሀይፖተርሚያ ሊጋለጡ እንደሚችሉ እና በህይወት ሊቆዩ የሚችሉት ጉዳት ባይደርስባቸውም ከአምስት እስከ 10 ሰአት ነው።
በቲቤት በኩል ቢያንስ 126 ሰዎች መሞታቸው እና 188 ሰዎች ደግሞ መጎዳታቸውን ሮይተርስ የቻይናውን የመንግስት ሚዲያ ሲሲቲቨን ዘግቧል። እንደዘገባው ከሆነ በኔፓል በሰው ህይወት ላይ ጉዳት ባይደርስም፣ ህንጻዎች ፈራርሰዋል፤ የኔፓል-ቲቤት ድንበር ዘግቷል።
800ሺ ሰዎች እንደሚኖሩባት በምትገመተው የቲቤት ሺጋሴ ግዛት ቢያንስ 3600 ቤቶች መወደማቸውን የመጀመሪያ ቆጠራ እንደሚያሳይ ሲሲቲቪ የአካባቢውን ባለስልጣናት ጠቅሶ ማክሰኞ ጠዋት ዘግቦ ነበር። ከ1800 በላይ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች እና 1600 ወታደሮች አደጋው ወደተከሰተበት ግዛት ተሰማርተዋል።
መንግስት ለአደጋው ተጋላጭ የሆኑ 30 ሺ ሰዎች አካባቢያቸውን ለቀው እንዲወጡ አድርጓል። ቻይና ከኔፓል ጋር በምትዋሰንበት ድንበር የምትገኘው ትንግሪ ደግሞ 60 ሺ ነዋሪዎች እንዳሏት ይገመታል።