የሳዑዲ አረቢያና ኢራን ስምምነት አሜሪካንን እንዳላስደሰተ ተገለጸ
አሜሪካ በስምምነቱ ያልተደሰተችው ሁለቱ ሀገራት በቻይና አደራዳሪነት በመስማማታቸው ነው ተብሏል
ሳዑዲ አረቢያ እና ኢራን በሁለት ወራት ውስጥ ኢምባሲዎቻቸውን ለመክፈት ተስማምተዋል
የሳዑዲ አረቢያ እና ኢራን አዲስ ስምምነት አሜሪካንን እንዳላስደሰተ ተገለጸ።
ላለፉት ሰባት ዓመታት በቀጥታ እና በእጅ አዙር ሲጠቃቁ የቆዩት ሳውዲ አረቢያ እና ኢራን ግንኙነታቸውን ለማሻሻል መስማማታቸው ይታወሳል።
ላለፉት አራት ቀናት በቤጂንግ ቻይና በድብቅ ሲደራደሩ የቆዩት ሪያድ እና ቴህራን በመጨረሻም ግንኙነታቸውን በፍጥነት ለማስተካከል ተስማምተዋል።
በዚህ ስምምነት መሰረት ሁለቱም ሀገራት በሁለት ወራት ውስጥ ኢምባሲዎቻቸውን እንከፍታለን ያሉ ሲሆን ስምምነቱ በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ ለነበሩ አለመረጋጋቶች መፍትሄ እንደሚመጣ ታምኖበታል።
ሁለቱ ሀገራት በመካከለኛው ምስራቅ የበላይነትን ለመያዝ የሚፎካከሩ ሲሆን አዲሱ ስምምነት ለየመን የእጅ አዙር ጦርነት እንዲያበቃ፣ የኢራን ኑክሌር ስምምነት እንዲደረግ እና ሌሎች አወንታዊ ሚናዎችን ያመጣል ተብሏል።
ይህ በዚህ እንዳለ ግን ሁለቱ ሀገራት በቻይና አደራዳሪነት ወደ ስምምነት መምጣታቸው ዋሸንግተንን እንዳላስደሰተ ሮይተርስ የቀድሞ የአሜሪካ እና ተመድ ዲፕሎማት የነበሩት ጄፍሪ ፌልትማንን አነጋግሮ ዘግቧል።
ዲፕሎማቱ እንዳሉትም "ስምምነቱ የቻይና ዓለም አቀፍ ተጽዕኖን የሚያጎላ እና ለፕሬዝዳንት ባይደን አስተዳድርን በጥፊ እንደመምታት ነው” ብለዋል።
በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የአስተዳድር ጊዜ የምስራቅ እስያ ዲፕሎማት የነበሩት ዳንኤል ሩሴል በበኩላቸው ቻይና ከዚህ በፊት ሀገራትን አደራድራ እንደማታውቅ የአሁኑ ድርጊትም ቻይና ተጽዕኖዋ እያደገ ለመሆኑም ማሳያ ነው ብለዋል።