ብሪታንያ በኢራን ጠቅላይ አቃቤ ህግ ላይ ማዕቀብ ጣላች
ቴህራን የብሪታንያ እና ኢራን ጥምር ዜግነት የነበራቸውን የቀድሞ ምክትል የመከላከያ ሚኒስትሯን በሞት መቅጣቷንም “አረመኔያዊነት” ነው ብላዋለች
አሊሬዛ አክባሪ ለብሪታንያ ሲስልሉ ነበር በሚል መገደላቸው ይታወሳል
ብሪታንያ በኢራን ዋና አቃቤ ህግ ጃፋር ሞንታዜሪ ላይ ማዕቀብ ጣላች።
ሞንታዜሪ ሃብታቸው እንዳይንቀሳቀስ የሚያደርግ እና የእንቅስቃሴ ገደብን የሚያስከትል ማዕቀብ ነው የተጣለባቸው።
ጠቅላይ አቃቤ ህጉ የብሪታንያ እና ኢራን ጥምር ዜግነት የነበራቸው የቀድሞ ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር እንዲገደሉ ትልቁን ድርሻ ውሰደዋል በሚል ነው ለንደን ማዕቀቡን የጣለችው።
አሊሬዛ አክባሪ ለብሪታያ በመሰለል እና በሙስና ወንጀል ተከሰው በሞት እንዲቀጡ በተወሰነ በቀናት ውስጥ መገደላቸውን ኢራን ማሳወቋ ይታወሳል።
ግድያውን “አረመኔያዊ” ነው ያለችው ብሪታንያ፥ በአሊሬዛ አክባሪ ላይ ለተፈጸመው የሞት ቅጣት ዋነኛው ተጠያቂ ባደረገችው ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጃፋር ሞንታዜሪ ላይ ማዕቀብ መጣሏን ሬውተርስ አስነብቧል።
የብሪታንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀምስ ክሌቨርሊ፥ “ሞንታዜሪ ኢራን በምታሳልፋቸው የሞት ውሳኔዎች እና ስር በሰደደው የሰብአዊ መብት ጥሰት ጉልህ ተሳትፎ እያደረጉ ነው” ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
በጠቅላይ አቃቤ ህጉ ላይ የተጣለው ማዕቀብም ብሪታንያ በአክባሪ ግድያ ክፉኛ መቆጣቷን እንደሚያሳይ ነው ሚኒስትሩ ያነሱት።
ብሪታንያ የአክባሪ ግድያ በየትኛውም መንገድ ሊወገዝ እንደሚገባ ገልጻለች።
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክም ግድያውን በጽኑ አውግዘውታል።
የብሪታንያ ዜግነት የነበራቸው አሊሬዛ አክባሪ “በአረመኔው የኢራን መንግስት” መገደላቸው እንዳስደነገጣቸው በመግለጽም በሀገሪቱ የሰብአዊ መብት ጥሰቱ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን በትዊተር ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
ብሪታንያ በኢራን ድርጊት መቆጣቷን ለመግለጽና ተጨማሪ ማብራሪያን ለመጠየቅ የኢራኑን አምባሳደር እንደምትጠራም መግለጿ የሚታወስ ነው።
ኢራን በመስከረም ወር 2022 በፖሊስ ቁጥጥር ስር የነበረችው ማሻ አሚኒ ከተገደለች በኋላ በአደባባይ ተቃውሞ እየተናጠች ነው።
የሀገሪቱ ባለስልጣናትም በሺዎች የሚቆጠሩ ለተቃውሞ የወጡ ዜጎችን በማሰር እና በሞት በመቅጣት ላይ ቢሆኑም ተቃውሞው ሊበርድ አልቻለም።
ቴህራን ተቃውሞዎችን አስተባብራለች ያለቻቸውን ቢያንስ 100 ሰዎች በሞት ለመቅጣት መዘጋጀቷ መገለጹም አይዘነጋም።