ቻይና ለዩንቨርሲቲ ተመራቂዎች እንደ ግዴታ ጥላው የነበረውን የእንግሊዘኛ ፈተና አስቀረች
ቻይናዊያን በዩንቨርሲቲው ውሳኔ ደስታቸውን እየገለጹ ነው
የቻይና ዩንቨርሲቲዎች የእንግሊዘኛ ፈተና ያላለፈ ተማሪን እያስመርቁም ነበር
ቻይና ለዩንቨርሲቲ ተመራቂዎች እንደ ግዴታ ጥላው የነበረውን የእንግሊዘኛ ፈተና አስቀረች፡፡
የዓለማችን ሁለተኛዋ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ቻይና ከፈረንጆቹ 1987 ጀምሮ ለመጀመሪያ ድግሪ ተማሪዎች የእንግሊዘኛ ፈተናን ማለፍ እንደግዴታ አስቀምጣለች፡፡
እንግሊዘኛ ፈተናን ያለፉ ተማሪዎችን ብቻ ስታስመርቅ የቆየችው ቻይና አሁን ግን ይህን እንደግዴታ መውሰድ በማቆም ላይ ትገኛለች፡፡
የቻይናው ጂያቶንግ ዩንቨርሲቲ ከዚህ በፊት ለመጀመሪያ ድግሪ ተማሪዎች እንደ ግዴታ ጥሎት የነበረውን የእንግሊዘኛ ቋንቋ ፈተና መቅረቱን አስታውቋል፡፡
ዩንቨርሲቲው ይህን ውሳኔ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ዌቦ የተሰኘው የቻይና ዋና የማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ቻይናዊያን ከሚወያዩበት ትልቁ አጀንዳ መካከል አንዱ ሆኗል፡፡
የዩንቨርሲቲወ ውሳኔ በርካታ ቻይናዊያንን አስደስቷል የተባለ ሲሆን ሌሎች ዩንቨርሲቲዎችም ውሳኔውን በቶሎ እንዲተገብሩ መወትወት ጀምረዋል፡፡
ከዚህ በፊት በርካታ ቻይናዊያን እንግሊዘኛ ቋንቋን ለመቻል የነበራቸው ጉጉት ከፍተኛ ነበር የተባለ ሲሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን ትኩረታቸውን እየቀነሱ መምጣታቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
የቻይና ግዙፍ የኢንዱስትሪ መዲና የሖነችው ሻንጋይ ከሁለት ዓመት በፊት እንግሊዘኛ ቋንቋ ለመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ፈተና እንዳይወስዱ መወሰኗ ይታወሳል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የቻይና ህግ አውጪ ምክር ቤት እና አማካሪዎች እንግሊዘኛ ቋንቋ ከቻይና ዩንቨርሲቲዎች እና ትምህርት ቤቶች እንደ ዋና የትምህርት አይነት እንዳይሰጥ ረቂቅ ህግ በማዘጋት ላይ እንደሆኑ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
እንዲሁም በቻይና ዩንቨርሲቲዎች ለመማር እንደ መግቢያ ፈተና እንዳይሰጥም ረቂቅ ህግ በመዘጋጀት ላይ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
እንግሊዘኛ ቋንቋ በቻይና ባሉ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንደ ማሟያ ትምህርት ብቻ እንዲሰጥ ማድረጓም ተገልጿል፡፡