ናይጀሪያ የእንግሊዘኛ ቋንቋ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዳይሰጥ አገደች
የአፍሪካ ባለ ግዙፍ ህዝብ ብዛት ባለቤት ናይጀሪያ ከ600 በላይ የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ባለቤት ናት
ናይጀሪያ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ብቻ እንዲማሩ የሚያዝ ፖሊሲ አውጥታለች
ናይጀሪያ የእንግሊዘኛ ቋንቋ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዳይሰጥ አገደች፡፡
ምዕራብ አፍሪካዊቷ ናይጀሪያ ከዚህ በፊት የእንግሊዘኛ ቋንቋ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ላሉ ተማሪዎች እንዲማሩ ስታደርግ ቆይታለች፡፡
ይሁንና አሁን ላይ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ከእንግሊዘኛ ቋንቋ ይልቅ በአፍ መፍቻ ቋንቋዎቻቸው እንዲማሩ መወሰኗን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የናይጀሪያ ትምህርት ሚኒስትር አዳሙ አዳሙ እንዳሉት አዲስ ብሄራዊ የቋንቋ ፖሊሲ መውጣቱን ገልጸው ህጻናት በትምህርት ቤቶች በሚቆዩባቸው የመጀመሪያዎቹ ስድስት ዓመታት በአፍ መፍቻ ቋንቋዎቻቸው እንዲማሩ መወሰኑን አክለዋል፡፡
እንግሊዘኛ ቋንቋ የናይጀሪያ የስራ ቋንቋ ሲሆን ሁሉም የትምህርት ተቋማት የማስተማሪያ እና መማሪያ ይፋዊ የስራ ቋንቋቸው ሆኖ በማገልገል ላይም ይገኛል፡፡
ናይጀሪያ የቋንቋ ፖሊሲ ያዘጋጀችው ህጻናት አፍ በፈቱበት ቋንቋቸው ቢማሩ የተሻለ እውቀት ማግኘት እንደሚችሉ በጥናት መረጋገጡን ተከትሎ እንደሆነም አስታውቃለች፡፡
ይሁንና በናይጀሪያ ከ600 በላይ የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ባለቤት መሆኗን ተከትሎ በነዚህ ቋንቋዎች ለማስተማር የሕትመት ወጪ፣ የሰለጠነ መምህር እና ሌሎች አቅርቦቶችን ማሟላት ሊፈትናት እንደሚችል ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡
እንዲሁም አዲስ በተዘጋጀው ብሄራዊ የቋንቋ ፖሊሲ ከመቼ ጀምሮ ወደ ተግባር እንደሚገባ አለመገለጹ ፖሊሲው ውጤታማ ላይሆን እንደሚችል ተሰግቷል፡፡