የቻይና እና ሩሲያ መሪዎች “ግንኙነታችን ለዓለም አቀፍ ግንኙነት አዲስ ምሳሌ ይሆናል” አሉ
የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂን ፒንግ ከሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር የቪዲዮ ውይይት አድርገዋል
ቻይና እና ሩሲያ በጋራ ፍላጎቶቻቸው ላይ ለመስራት ከ20 ዓመት በፊት ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል
የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂን ፒንግ ከሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር የቪዲዮ ውይይት ማድረጋቸውን አስታወቁ።
የቻይና ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት የሁለቱ ሀገሮች ፕሬዝዳንቶች የቤጅንግ እና ሞስኮን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችል ውይይት ማድረጋቸውን አስታውቋል።
ፕሬዝዳንቶቹ፤ ቻይና ሩሲያ ከ 20 ዓመት በፊት የተተፈራረሙት የመልካም ጉርብትናና የወዳጅነት ትብብር እንዲቀጥል መስማማታቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል።
የሞስኮ እና የቤጅንግ ትብብር ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አወንታዊ ሃይል እንደሆነም በውይይቱ መገለጹ ይፋ ሆኗል።
የቻይናው ፕሬዝዳንት የሰው ልጅ በርካታ ችግሮች እየገጠሙት ባለበት በዚህ ወቅት የሁለቱ ሀገራት ትብብር ለዓለም አቀፍ ግንኙነት አዲስ ምሳሌ ይሆናል ማለታቸው ተገልጿል።
ሀገራቱ በጋራ ፍላጎቶቻቸው ላይ ለመስራት ከ20 ዓመት በፊት ስምምነት ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን ይህም ለዓለም አቀፍ ግንኙነት አዲስ በር እንደሚከፍት ሁለቱም መሪዎች አንስተዋል ተብሏል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ 100ኛ ዓመት እንኳን አደረሳችሁ ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን ፤ ሞስኮ እና ቤጅንግ ከመንግስት ለመንግስት ግንኙነት ባለፈም የፓርቲ ለፓርቲ ግንኑነት እንደሚኖራቸውም ፍንጭ ሰጥተዋል።
ቤጂንግ በኮሙኒስት ፓርቲዋ እየተመራች አዳዲስ ለወጥ እንደምታመጣ እርግጠኛ መሆናቸው የገለጹት ቭላድሚር ፑቲን፤ በማህበራዊ ዕድገት በኩል አዲስ ነገር እንደምታመጣና ይህም በዓለም አቀፍ ግንኙነት ትልቅ ሚና እንደሚኖረው አንስተዋል።
ሁለቱ ፕሬዝዳንቶች ባደረጉት ውይይት በአውሮፓ ሕብረት እና በሩሲያ መካከል ሊደረግ የነበረው ውይይት መሰረዙም ይፋ ሆኗል።
የአውሮፓ ሕብረት አባል ሀገራት ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ጋር ለመወያየት ዕቅድ ቢይዙም ውይይቱ ግን መቅረቱ ተገልጿል፤ ክሬሚሊን ሊደረግ ታስቦ የነበረው ውይይት መቅረቱ አሳዛኘ እንደሆነ አስታውቋል።