ልዩልዩ
ቻይና እና ሩሲያ ጨረቃ ላይ ዓለም አቀፍ የምርምር ጣቢያ ለማቋቋም ተስማሙ
ፍላጎቱ ያለው የትኛውም ሃገር በውጥኑ ሊሳተፍ እንደሚችልም ሃገራቱ አስታውቀዋል
ጣቢያው በጨረቃ ላይም ሆነ ከጨረቃ ውጭ ምርምሮችን ለማድረግ የሚያስችል ነው ተብሏል
ጨረቃ ላይ ዓለም አቀፍ የምርምር ጣቢያ ለማቋቋም የሚያስችል ስምምነት ከሩሲያ ጋር ማድረጉን የቻይና ብሔራዊ ጠፈር አስተዳደር አስታወቀ፡፡
በሃገራቱ መንግስታት የጸደቀው የስምምነት ሰነድ በአስተዳደሩ ኃላፊ ዣንግ ኬዢያን እና በሩሲያ አቻቸው ዲሚትሪ ሮጎዚን በበይነ መረብ ተፈርሟል፡፡
ሰነዱ በጣቢያው ግንባታ እና ሌሎችም ተያያዥ ሂደቶች ለመተባበር የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡
ውጥኑ ሳይንሳዊ የመረጃዎች ልውውጥን ለማሳደግ እና ሰላማዊ የጠፈር አሰሳ እና ተጠቃሚነት ተነሳሽነትን የበለጠ ለመፍጠር እንደሚያስችል ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
የትኛውም ፍላጎቱ እና ዝግጁነቱ ያለው ሃገር በውጥኑ ሊሳተፍ እንደሚችልም ነው የሃገራቱን ባለስልጣናት መግለጫ ዋቢ ያደረገው የግሎባል ታይምስ ዘገባ የጠቆመው፡፡
ጣቢያው በጨረቃ ላይ ወይም ከጨረቃ ውጭ ሊደረጉ ለሚችሉ ምርምሮች የረዥም ጊዜ አገልግሎት ይኖረዋልም ተብሏል፡፡
ሃገራቱ በህዋ ሳይንስ እና ጠፈር ቴክኖሎጂ ያላቸውን የካበተ ልምድ በመጠቀም ጣቢያውን ለመገንባት፣ የጋራ እቅድ፣ ዲዛይን ለማዘጋጀት እና ለመተግበር በቅርበት በቅንጅት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡