"ድምፃችን ለነፃነታችንና ለሉዓላዊነታችን" በሚል በተካሔደው ሰልፍ ላይ ሩሲያ እና ቻይና ተመሰገኑ
ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በክልሎችም የውጭ ጣልቃ ገብነትን በመቃወም ሰልፎች ተካሒደዋል
“የአሸባሪውን ህወሓት እጅ መቁረጥ ድጋፍ የሚያሰጥ ቢሆንም ተቃውሞ ቀርቦብናል”- ወ/ሮ አዳነች አቤቤ
የውጭ ጣልቃ ገብነትን በመቃወም "ድምፃችን ለነፃነታችንና ለሉዓላዊነታችን" በሚል መሪ ሀሳብ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በተለይም ወጣቶች ዛሬ ሰልፍ አድርገዋል፡፡
የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት እንዲሁም በታላቁ የሕዳሴው ግድብ ግንባታና ሁለተኛውን የውሃ ሙሌት አስመልክቶ እየተፈጠሩ ያሉ ጫናዎችን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በአዲስ አበባ ስታዲየም ነው የተካሔደው።
የከተማዋ ነዋሪዎች የውጭ ጣልቃ ገብነትን ባወገዙበት በዚህ ሰልፍ ላይ የሩሲያ እና የቻይናን ፕሬዝደንቶችን ምስል በአደባባይ ይዘው የወጡ ሲሆን ፣ ሩሲያ እና ቻይና ከኢትዮጵያ ጎን በመቆማቸው ምስጋና ስለማቅረባቸው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል።
ሩሲያ እና ቻይና በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ ላይ በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ሊወጣ ታስቦ የነበረውን የጋራ የውሳኔ ሀሳብ በመቃወም ከኢትዮጵያ ጎን መቆማቸው ይታወሳል፡፡
በአዲስ አበባ ስታዲየም በነበረው ሰልፍ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ለሚደረግብን ጫና “አንበረከክም” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
“እኛ ኢትዮጵያዊያን ማንንም ለመጉዳት እንደማንፈልግ ሁሉ ማንም እንዲጎዳን አንፈቅድም” ያሉት ወ/ሮ አዳነች አክለውም “በራሳችን ወጪ የምንገነባውን ግድባችንን ለማስቆም ያልፈነቀሉት ድንጋይ ያልሸረቡት ሤራ የለም፤ ነገር ግን አይሳካላቸውም” ብለዋል፡፡
“የአሸባሪውን ህወሓት እጅ መቁረጥ ድጋፍ የሚያሰጥ ቢሆንም ተቃውሞ ቀርቦብናል” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የአሜሪካ መንግስት የጣለውን የቪዛ ክልከላ ዳግም እንዲያጤነውም ነው የጠየቁት፡፡
ኢትዮጵያውያን ጫናዎችን መቋቋም እና ማሸነፍ የሚችሉት በጋራ መሆኑን አውቀው “ልዩነቶችን እና የእርስ በእርስ መጠራጠሮችን” በመተው በአንድነት እንዲቆሙም ምክትል ከንቲባዋ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
"ድምፃችን ለነፃነታችንና ለሉዓላዊነታችን" በሚል መሪ ሀሳብ ፣ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎችም ሰልፎች ተካሂደዋል፡፡
የአሜሪካ መንግስት ፣ በትግራይ ክልል ለተፈጠረው ግጭት ተጠያቂ ናቸው ባላቸው የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ባለስልጣናት እና ወታደራዊ አመራሮች ላይ የቪዛ እገዳ መጣሉ ይታወሳል፡፡ አሜሪካ የኢኮኖሚ እና የጸጥታ ድጋፍ እገዳም የጣለች ሲሆን ፣ ችግሩን በውይይት በመፍታት አፋጣኝ እልባት መስጠት ካልተቻለ ተጨማሪ እገዳዎችን እንደምትጥልም አስታውቃለች፡፡ ይህ የአሜረካ ድርጊት የኢትዮጵያን እና የኤርትራን ባለስልጣናት ክፉኛ አስቆጥቷል፡፡