አሜሪካ በሰሜን ኮሪያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል ያቀረበችውን ረቂቅ ሩሲያና ቻይና አዘገዩባት
አሜሪካ በተደጋጋሚ የሚሳኤል ሙከራዎች ምክንያት ነው ሰሜን ኮሪያ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል የጠየቀችው
ሰሜን ኮሪያ በአንድ ወር ውስጥ 7 የሚሳዔል ሙከራዎችን አድርጋለች
ዋሸንግተን በፒንግያንግ ላይ ማዕቀብ ለመጣል ሃሳብ ብታቀርብም ቤጅንግ እና ሞስኮ እንዳዘገዩባት ተገለጸ።
አሜሪካ ከሰሞኑ ሰሜን ኮሪያ በተደጋጋሚ የሚሳኤል ሙከራ ማድረጓን መነሻ በማድረግ ነው ማዕቀብ ለመጣል ሃሳብ ያቀረበችው።
በዚህም መሰረት አምስት ሰሜን ኮሪያውያን ላይ የጉዞ ማዕቀብ እንዲጣልባቸው አሜሪካ ፍላጎት እንዳላትና ይህንንም ረቂቅ በማዘጋጀት ለተመድ ፀጥታው ምክር ቤት እንዲቀርብ እየሰራች ነበር ተብሏል።
በጉዳዩ ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ዝግ ስብሰባ ከማካሄዱ አስቀድሞ ቻይናና ሩሲያ ለአሜሪካ ረቂቅ ምላሽ ሰጥተዋል።
ቤጅንግ በሰሜን ኮሪያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል ጊዜ እንደሚያስፈልግ እና ጉዳዩ በደንብ መጥናት እንደሚገባው የገለጸች ሲሆን፤ ሩሲያ ደግሞ አሜሪካ ያቀረበችውን ረቂቅ ለመደገፍ በቂ ማስረጃ እንደሚያስፈልግ በመግለጽ መመለሳቸው ሮይተርስ ዘግቧል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ያላቸው ሩሲያ እና ቻይና ያዘገዩት የሰሜን ኮሪያን አምስት ዜጎች ማዕቀብ የመጣል ሃሳብ እስከ ስድስት ወር ሊቆይ እንደሚችል ተገልጿል።
አሜሪካ ሰሜን ኮሪያውያን ላይ ማዕቀብ ለመጣል ያዘጋጀችው ረቂቅ ልክ እንደ ሩሲያ እና ቻይና በድጋሚ ሌላ የፀጥታው ምክር ቤት አባል ሀገር ጥያቄ የሚኒሳበትና የሚዘገይ ከሆነ ለሶስት ወራት ይቆይ ከውይይት ጠረንጴዛ ላይ እንደሚነሳ የተመድ ሕግ ያዛል።
የተመድ ፀጥታው ምክር ቤት ቋሚና ተለዋጭ አባላት የሆኑት አሜሪካ፣ አልባኒያ፣ ብራዚል፣ ፈረንሳይ፣ አይርላንድ፣ የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች፣ ብሪታኒያ እና ጃፓን በጋራ ባወጡት መግለጫ ሰሜን ኮሪያ የምታስወነጭፋቸው ሚሳኤሎች፤ ፒዮንግያንግ ጅምላ ጨራሽ መሳሪያንና ባልስቲክ ሚሳኤልን ወደቀድሞው ሁኔታ ለመመለስ እየሰራች መሆኑን በመግለጽ ተቃውመዋል።
ሀገራቱ ሰሜን ኮሪያ ጅምላ ጨራሽ መሳሪያንና ባልስቲክ ሚሳኤልን በየትኛውም መንገድ ለመመለስ እየሰራች መሆኗንና ይህንን የምታደርገውም በሰሜን ኮሪያውያን ኪሳራ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
አሜሪካ በበኩሏ የተመድ ፀጥታው ምክር ቤት በፒዮንግያንግን ላይ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ ጠይቃለች።