ሰሜን ኮሪያ ከ2017 ወዲህ ግዙፍ የተባለ የሚሳዔል ሙከራ ማድረጓ ተገለፀ
800 ኪሎ ሜትር ተጉዟል ተባለው ሚሳዔሉ ለ30 ደቂቃ ያክል መብረሩም ታውቋል
አሜሪካ፣ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ አዲሱን የሰሜን ኮሪያ የሚሳዔል ሙከራ አውግዘዋል
ሰሜን ኮሪያ ከፈረንጆቹ 2017 ወዲህ ግዙፍ የተባለለት የሚሳዔል ሙከራ በዛሬው እለት ማድረጓ ተሰምቷል።
የጃፓን እና የደቡብ ኮሪያ ባለስልጣናት እንዳስታወቁት ሰሜን ኮሪያ በዛሬው እለት ያስወነጨፈችው ሚሳዔል በ2000 ኪሎ ሜትር ከፍታ ለ30 ደቂቃ አየር ላይ መብረር ችሏል።
አዲሱ የሰሜን ኮሪያ ሚሳዔል 800 ኪሎ ሜትር ያክል ከተጓዘ በኋላ በጃፓን ባህር ውስጥ መውደቁንም ባለስልጣናቱ አስታውቀዋል።
የደቡብ ኮሪያ የዜና ተቋም ዮናፕ እንደዘገበው፤ ሰሜን ኮሪያ በዛሬው እለት ያካሄደችው የሚሳዔል ሙከራ ሀገሪቱ በ2017 ካካሄደችው ሀዋሶንግ 12 ከሚባው ሚሳዔል ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው።
የአሜሪካ መንግስት ሰሜን ኮሪያ ከእንዲዚህ አይነት ፀብ አጫሪ ድረጊቶች እንድቶጠብ አሳስቧል።
ሰሜን ኮሪያ የዛሬውን ጨምሮ በዚህ ወር ብቻ ሰባት የአጭር እና የረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳዔሎች ሙከራን ያደረገች ሲሆን፤ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ እና አሜሪካ ተግሩን አውግዘዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ሰሜን ኮሪያ የባልስቲክ ሚሳኤል ሙከራዎችን ከማድረግ እንድትቆጠብ በተደጋጋሚ በማሳሰብ ማዕቀብ መጣሉ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ ፒዮንግያንግ የተመድ የጸጥታው ምክር ቤትን ማስጠንቀቂያ ችላ በማለት የምታደርገውን የባልስቲክ ሚሳኤል ሙከራ ለማስቆም በሀገሪቱ ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦችን መጣል እንደሚስፈልግ ተንታኞች እየተናገሩ ነው።