የሰሜን ኮሪያ በይነ መረብ ጠላፊዎች በ2021 ዓመት 400 ሚሊየን ዶላር መዝረፋቸው ተገለጸ
ጠላፊዎቹ ገንዘቡን የመዘበሩት በኢንቨስትመንት ተቋማት ላይ ባደረጓቸው ሰባት የበይነ መረብ ጥቃቶች ነው
ሰሜን ኮሪያ በበኩሏ ስለ ጠላፊዎቹ የማውቀው ነገር የለም ብላለች
የሰሜን ኮሪያ የበይነ መረብ ጠላፊዎች በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2021 ዓመት 400 ሚሊየን ዶላር ዋጋ ያለው የዲጂታል ገንዘብ መዝረፋው ተገለጸ።
የምስራቅ እስያ ኩባንያዎች ዋነኞቹ የሰሜን ኮሪያ በይነ መረብ መዝባሪዎች ኢላማ እንደነበሩም ተነግሯል።
የብሎክቼይን ወይም የድጅታል ገንዘብ ጉዳዮችን በመተንተን የሚታወቀው ቼይንናላሲስ እንዳለው የተጠናቀቀው 2021 ዓመት የድጅታል መገበያያ ገንዘብ ምዝበራ ወንጀሎች የተመዘገቡበት ዓመት ነበር ብሏል።
ተቋሙ እንዳሳወቀው በ2021 ዓመት ምስራቅ እስያ አካባቢ የጠላፊዎች ዋነኛ የትኩረት ማዕከል የነበሩ ሲሆን፤ በተለይም የኢንቨስትመንት ተቋማት የገንዘብ ዝውውሮች የጠላፊዎቹ አይን ማረፊያ ናቸው ተብሏል።
ይሁንና ሰሜን ኮሪያ በተቋሙ የቀረበባትን ክስ ውድቅ ያደረገች ሲሆን፤ ስለ ጉዳዩ የምታውቀው ነገር እንደሌለ ገለልጻለች።
የሰሜን ኮሪያ በይነ መረብ ጠላፊዎች በፈረንጆቹ 2020 ዓመት አራት ብቻ የነበረ ሲሆን፤ በ2021 ዓመት ደግሞ ቁጥሩ ወደ ሰባት ከፍ ማለቱንም ዘገባው አክሏል።
ጠላፊዎቹ የኢንቨስትመንት ተቋማትን ለመጥለፍ የተለያዩ ስልቶችን ይጠቀማሉ የተባለ ሲሆን፤ የተቋማቱን መግባቢያ ኮዶችን መስረቅ፣ቫይረሶችን መልቀቅ እና ሌሎች ቴክኒኮችን በመጠቀም ወደ ሰሜን ኮሪያ ተቋማት ያዘዋውራሉም ተብሏል።
የበይነ መረብ መገበያያ ገንዘቦች ከኢንተርኔት ጋር የተቆራኙ መሆናቸው ለበይነ መረብ ጠላፊዎች ተጋላጭ ሊሆኑ እንደቻሉም ዘገባው አክሏል።
በ2021 ዓመት ከተካሄዱ የበይነ መረብ ጠለፋዎች መካከል አብዛኞቹ የተካሄደው በአሜሪካ ማዕቀብ የተጣለበት ላዛሩስ የተሰኘው የበይነ መረብ መንታፊዎች ቡድን ነው ተብሏል።
ይህ የመንታፊዎች ኩባንያ ንብረትነቱ የሰሜን ኮሪያ መንግስት የደህንነት ቢሮ እንደሆነ የሚጠረጥር ሲሆን፤ ከዚህ በፊት ‘ዋናክራይ’ የተሰኘ ቫይረስ በዓለም አቀፍ ባንኮች ላይ እና መሰረተ ልማቶች ላይ በመልቀቅ ገንዘብ እና መረጃዎችን በመመንተፍ ይታወቃል።
ሰሜን ኮሪያ በበይነ መረብ መንታፊዎች አማካኝነት የምታገኘውን ገንዘብ ለሚሳኤል ልማት እያዋለች በመሆኑ ከድርጊቷ እንድትታቀብ ተመድ አስጠንቅቋል።
አሜሪካ ባሳለፍነው የካቲት በሶስት የሰሜን ኮሪያ የኮምፒዩተር ማቀላጠፊያ አልሚዎች 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር መሰረቋን እና በነዚህ ባለሙያዎች ላይ ክስ መመስረቷን አስታውቃ ነበር።