ከምዕራባውያን ጋር ፍጥጫ ውስጥ የገባችው ሩሲያ ከቻይና ጋር አዲስ የጋዝ ማስተላለፊያ ስምምነት አደረገች
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቤጂንግ ይገኛሉ
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከቻይናው አቻቸው ሺ ጂን ፒንግ ጋር ተወያይተዋል
በዩክሬን ጉዳይ ከአሜሪካ እና ከአጋሮቿ ጋር ውጥረት ውስጥ የገባችው ሩሲያ ከቻይና ጋር ጋዝ የማስተላለፊያ አዲስ ስምምነት ማድረጓ ተገለጸ።
ሞስኮ እና ቤጅንግ አዲስ የነዳጅ ስምምነት ያደረጉት ዛሬ የሩሲያ ፕሬዝዳንት ለጉብኝት ቻይና ከገቡ በኋላ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
የበጋ ኦሊምፒክን እያዘጋጀች ባለችው ቻይና ጉብኝት እያደረጉ ያሉት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከቻይናው አቻቸው ሺ ጂን ፒንግ ጋር መወያየታቸው ተሰምቷል።
ሁለቱ መሪዎች ባደረጉት ውይይት ሞስኮ ከቤጅንግ ጋር አዲስ የጋዝ ማስተላለፊያ ስምምነት መፈጸሟ ይፋ ሆኗል። ሩሲያ የቻይና ሶስተኛዋ ጋዝ አቅራቢ ብትሆንም ዛሬም አዲስ የአጋርነት ስምምነት ተፈራርመዋል።
ሞስኮ ከቤጅንግ ጋር የተስማማችው አዲስ የጋዝ ስምምነት የጋዝ ግብይቷ በአውሮፓ ደንበኞች ላይ ብቻ የተንጠለጠለ እንዳይሆን እንደሚያግዛት ነው የተጠቀሰው።
የሩሲያ እና የቻይና መሪዎች ባደረጉት ውይይት ትብብርን በማጠናከር ላይ ትኩረት ማድረጋቸውን ቭላድሚር ፑቲን ተናግረዋል።
ፑቲን “የእኛ ባለሙያዎች ለቻይና ነዳጅን በአዲስ መልክ ለማቅረብ ዝግጅት አድርገዋል” ሲሉ መናገራቸውም ተሰምቷል።
አሁን ሁለቱ ሀገራት ያደረጉት ስምምነት በጋዝ ኢንዱስትሪ ውስጥ ወደፊት መጓዝን እንደሚያመለክት የተገለጸ ሲሆን፤ በዚህም 10 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ጋዝ ለቻይና ማቅረብ ያስችላል።
የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅትን (ኔቶ) ለመቀላቀል ፍላጎት ባላት ዩክሬን እና በሩሲያ መካከል ያለው ውጥረት በተጋጋለበት ሁኔታ ነው ፑቲን ቤጅንግ የገቡት።
ሩሲያ የአውሮፓ ትልቋ ጋዝ አቅራቢ ስትሆን በሩሲያ እና በዩክሬን ድንበር ባለው ውጥረት ይህ አቅርቦት እንዳይቋጥ ስጋት አላቸው ተብሏል።
ሞስኮ እና ቤጅንግ ያደረጉት አዲሱ ስምምነት ሩሲያ ወደ አውሮፓ ትልከው የነበረውን ጋዝ አያስቀረውም ተብሏል፡።
የሩሲያ ግዙፍ የጋዝ ኩባንያ ጋዝፕሮም ለቻና 48 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ጋዝ እንደሚላክ ገልጸዋል።