ቻይናና ሩሲያ የባህር ኃይሎች ግዙፍ የሆነ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ መጀመራቸውን አስታወቁ
በልምምዱ ላይ አውዳሚ የሆኑ የቻይናና የሩሲያ ግዙፍ የጦር መሳሪያዎች እየተሳተፉ ተብሏል
ሩሲያና ቻይና የባህር ኃይሎች ወታራዊ ልምምድ የጀመሩት “ጠብ አጫሪ ነው” ያሉት የኔቶ ጉባዔ መጠናቀቁን ተከትሎ ነው
የቻይና እና የሩሲያ የባህር ኃይሎች የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ማድረግ መጀመራው ተነግሯል።
ቻይና እና ሩሲያ በደቡብ ቻይና ዣንጂያንግ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ በውሃ እና በአየር ክልል ላይ የጋራ የባህር ሀይል ልምምዶችን እያደረጉ መሆኑን ትናንት አርብ አስታውቀዋል።
“የጋራ ባህር-2024” በሚል መጠሪያ የተሰጠው ልምምዱ በሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ የተጀመረ ሲሆን እስከ ወሩ አጋማሽ ድረስ እንደሚቆይ የቻይና መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የሁለቱ ሀገራት የባህር ኃይል የጋራ ልምምድ ላይ አውዳሚው የጋይድድ ሚሳዔልን ጨምሮ ሌሎችም ግዙፍ መሳሪያዎችን የታጠቁ የጦር መርከቦች እንደሚሳተፉ ነው የተገለጸው።
የቻይና መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዣንግ ዢያኦጋንግ "ልምምዱ ሁለቱ ወገኖች የባህር ላይ የጸጥታ ስጋቶችን በጋራ ለመቅረፍ እንዲሁም አለም አቀፍ እና ቀጠናዊ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ያላቸውን ቁርጠኝነት እና አቅም ለማሳየት ያለመ ነው" ብለዋል።
“የጋራ ባህር-2024” በሚል መጠሪያ የተሰጠው ልምምዱ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረሰው መደበኛ የመከላከያ ትብብር አካል መሆኑንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
አዲሱ የባህር ኃይሎች ልምምድ “በአዲሱ ዘመን የቻይና-ሩሲያ አጠቃላይ ስትቴጂካዊ የትብብር አጋርነትን የበለጠ ያጠናክራል” ብለዋል ዣንግ።
የቻይና እና የሩሲያ የባህር ኃይሎች የጋራ ወታደራዊ ልምምድ የታወጀው በዋሽንግተን በተደረገው የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) ስብሰባ መጠናቀቁን ተከትሎ ነው።
በዋሽንግተኑ የኔቶ ስበሰባ ላይ የተሳተፉ ሀገራት በቻይናና በሩሲያ መካከል ያለው ስትራቴጂካዎ አጋርነት እንዲሁም ሁለቱ ሀገራት ለመፍጠር እየሰሩት ያለው አዲስ የዓለም ስርዓት ትልቅ ስጋትን የሚደቅን መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።
ቻይና የኔቶ መግለጫ "በቀዝቃዛው ጦርነት አስተሳሰብ እና በጦር አነጋገር የተሞላ ነው" ስትል ተችታለች።